ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 2 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ዛሬ ጅግጅጋ ገብተዋል።

ርዕስ መስተዳድሩ ጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አየር ማረፍያ ሲደርሱ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስታዳድር ርአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ የልዑካን ቡድን በጅግጅጋ ከተማ ተገኝቶ ድጋፉን ለሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ኡመር አስረክቧል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በድጋፉ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ ድርቅ ያጋጠመ ቢሆንም ድጋፉ የክልሉ መንግሥት ለወንድም የሶማሌ ህዝብ ያለውን አጋርነት ያሳየበት ነው።

ሁለቱ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍ በአጎራባች ወረዳዎች በመስኖ ልማት እና በእንስሳት መኖ ላይ በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሽመልስ እንዳሉት በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመቋቋም የጀመሯቸውን የልማት ስራዎች በጋራ አጠናክረው ይቀጥላሉ።

የኦሮሚያ ክልልል ሕዝብና መንግሥት ወንድም ለሆነው የሶማሌ ህዝብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።

የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተደድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዛሬው እለት በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ በሰመራ ከተማ አንድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም