ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ የሀሳብ ልዩነትን በማቀራረብ ዘላቂ ሰላም ያመጣል -የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

ነገሌ የካቲት 2/2014/ ኢዜአ /በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር የሀሳብ ልዩነቶችን በማቀራረብ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያስችላል ሲሉ በጉጂ ዞን አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች አመለከቱ።
በሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ለሰላም እጁን እንዲዘረጋ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የምክክር መድረኩ የሀሰብ ልዩነትን በማቀራረብና የጋራ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያስችላል የሚል ተስፋ ማድረጋቸውን አስተያየት ሰጭዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል ።

የጉጂ ኦሮሞ እጩ አባገዳ ሳሙኤል ቦሩ እንደገለጹት በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ሁሉንም ዜጎች በማሳተፍ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የተያዘው እቅድ የሚደገፍ ነው፡፡

በመቻቻል፣ በመከባበርና በመደማመጥ የምክክር መድረኩን ለብሄራዊ መግባባትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል፡፡

"የኢትዮጵያ መሬት ሰፊና ለሁላችንም የሚበቃ በመሆኑ ብሄራዊ መግባባት፣ ሰላምና ፍቅር ካለ ከእራሳችን አልፈን ለሌላም እንተርፋለን" ብለዋል ፡፡

የጥላቻና ቂም በቀል አስተሳሰብ ትርፉ የእርስ በእርስ ግጭት፣ ስደትና መፈናቀል፤ ከዚያም አለፍ ሲል ሀገር ማፍረስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

"ቤተሰብ መስርቶ ሀብት አፍርቶ  መኖር የሚቻለው ሀገር ሰላም ሲሆን በመሆኑ ሁላችንም ለብሄራዊ መግባባት ቅድሚያ እንስጥ" ብለዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ መቶ አለቃ አበራ ጀምበሩ የምክክሩ መድረኩ በአንድ ሀገር ልጆች መካከል የሚደረግ በመሆኑ ከቂምና ጥላቻ የጸዳ እንዲሆን መክረዋል፡፡

የሀሳብ ልዩነት  ለዜጎች ስደትና መፈናቀል ምከንያት ሊሆን እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡

በሀገራዊ መግባባት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲመጣ አለመግባባትን በውይይት የመፍታት ባህል ሊለመድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሀሳብ ልዩነትን በሰለጠነ አስተሳሰብ በመፍታት ሀገርን ከውጭ ጫናና ጣልቃገብነት መከላከል የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

 የሀይማኖት አባትና የነገሌ ከተማ ነዋሪ መምሬ አፈወርቅ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው "እኔ ካልመራሁ ሀገር ይፈርሳል የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ሊታረም ይገባል" ብለዋል፡፡

"ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የምክክር መድረኩን የሚመሩ ሀገርንና ሰላምን ብቻ የሚያስቀድሙ ከማንኛውም ወገንተኝነት ነጻና ገለልተኛ ሊሆኑ ይገባል" ሲሉም አመልክተዋል።

የግል ስሜትና ፍላጎቶችን በመግታት ባንጻሩ የመቻቻልና የእኩልነት ባህልን በማጎልበት የበለጸገች ሀገር ለመገንባት መትጋት እንደሚገባ መክረዋል ።

"ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ጥንት የነበረው አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር እንዲመለስ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመቻቻል፣ የፍቅርና የአንድነት ሀገር እንደመሆኗ  የሀሳብ ልዩነትና አለመግባት በውይይት የሚፈታበት ባህላዊ አሰራር  ጭምር ያለት ሀገር መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም