ቀጥታ፡

አባቴ ከሀብት በላይ የሆነውን የሀገር ፍቅር አውርሶኛል

የካቲት 2/2014/ኢዜአ “አባቴ ከሀብት በላይ የሆነውን የሀገር ፍቅር አውርሶኛል” ሲል ለሀገሩ በጀግንነት የተሰዋው፤ በዚህም አንደኛ ደረጃ “የላቀ ጀግና” የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው የሻለቃ እያሱ ሽመልስ ልጅ አማኑኤል እያሱ ተናገረ።

ሻለቃ እያሱ ላብ ከደም ገብሮ ሀገርን በክብር ለማቆም የቆረጠ፣ በእጅ ቦንብ የጠላትን ታንክ የማረከ፣ ለሀገሩ በክብር የተሰዋ ጀግና ነው።

መንግሥት በሕልውና ዘመቻው ለተሰዉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የመታሰቢያ መርኃ ግብርና በጦር ሜዳ የላቀ ጀብድ ለፈጸሙ አባላት የላቀ ጀግና ሜዳሊያ ሽልማት ማበርከቱ ይታወሳል።

ከእነዚህ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በጦር ግንባር ህይወቱ ያለፈው ሻለቃ እያሱ ሽመልስ በቅጽል ስሙ (ጅቦ) አንዱ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ የላቀ ጀግና ሜዳልያ ተሸላሚ ነው።

ሻለቃ እያሱ የአሸባሪውን ህወሃት ቡድን በከፍተኛ ጀግንነት ተፋልመው መቀሌን ከተቆጣጠሩት የኮማንዶ አመራሮች መካከል አንዱ ነበር።

በኋላም አሸባሪው ህወሃት አገር ለማፍረስ በከፈተው ጦርነት ኮማንዶ ሻለቃውን በመምራት በመርሳ ግንባር በጀግንነት ተዋግቷል፤ አዋግቷል።

በእጅ ቦንብ የጠላትን ታንክ የማረከ ጀግና መሆኑም በሽልማቱ ወቅት ተገልጿል።

የሻለቃ እያሱ ቤተሰቦችም መንግሥት ለተሰዉ ጀግኖች እንደዚህ አይነት ሽልማት መስጠቱና ጀግንነታቸውን ማውሳቱ ሞታቸውን እንዳናስብ አድርጎናል ሲሉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የሻለቃ እያሱ ባለቤት ወይዘሮ ማርታ ዳምጤ፤ "ባለቤቴ አገር ወዳድና ከቤተሰቡ በፊት አገርን የሚያስቀድም ነበር" ብለዋል።

የወታደር ቤተሰብ መሆን ትልቅ ክብር መሆኑን በመጥቀስ ባለቤታቸው ሻለቃ እያሱ በፈጸመው ጀብድ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የሻለቃ እያሱ ልጅ አማኑኤል እያሱ በበኩሉ አባቴ  ከሀብት በላይ የሆነውን የሀገር ፍቅር አውርሶኛል ብሏል።

"አባቴ ሲያሳድገኝ አገር ወዳድ ሆኜ እንዳድግና ሰው ለሆነ ፍጥረት በሙሉ አንድ አይነት አመለካከት እንዲኖረኝ አድርጎ ነው" የሚለው አማኑኤል በአባቱ ጀግንነት ሁልጊዜ እንደሚኮራ ተናግሯል።

ሻለቃ እያሱ በሥራ ባልደረቦቹ ዘንድ "ጅቦ" በሚል ቅጽል ሥም እንደሚጠራ ያስታወሱት ወይዘሮ ማርታ የባለቤታቸው ጀግንነት በቃላት የማይገለጽ መሆኑን ተናግረዋል።

ሻለቃ እያሱ ሽመልስ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በአገር መከላከያ የልዩ ኮማንዶ አባል በመሆን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተሳትፏል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚሰጠውን አገራዊ ግዳጅ በብቃት በመፈጸም የሚታወቅ ሲሆን ከአገር ውጪም በተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ አገልግሏል።

ሻለቃ እያሱ በሥራ ባልደረቦቹ በሥራ ሃላፊዎቹ ዘንድ እምነት የሚጣልበት ልበ ሙሉ ቆራጥ ጀግና እንደነበር ብዙዎች ይመስክሩለታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም