በሰቆጣ ከተማ አቅራቢያ ትናንት ምሽት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

66
ሰቆጣ ግንቦት 10/2010 በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በሰቆጣ ከተማ አቅራቢያ ትናንት ምሽት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ትናንት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ በደረሰው አደጋ  27 ሰዎችም   ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የመንገድ ደህንነት ትራፊክ የስራ ሂደት ተወካይ ሳጅን ሸጌ መንግስቴ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው 30 ኩንታል ስንዴ የጫነ አይሱዙ መኪና ከጭነቱ በላይ 31 ሰዎችን አሳፍሮ ከሰቆጣ ከተማ ወደ ዙሪያ ወረዳ ሲጓዝ በነበረበት ወቅት ነው። የመገልበጥ አደጋው ከከተማው ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ  ሸሸረን በሚባል ቦታ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ኮድ 3 -28996 አዲስ አበባ የሆነው አይሱዙ የጭነት መኪና ከህግ ውጭ በሆነ መንገድ ሰውን ከእቃ ጋር ደርቦ በመጫኑ አደጋውን የከፋ እንዳደረገው ተናግረዋል። ከሞቱት መካከል 3ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልፀው የሟቾች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መላኩን አስታውቀዋል፡፡ በአደጋው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በአሁኑ ወቅት በሰቆጣ ተፈራ ሐይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል። የመኪናው አሽከርካሪ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት  መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ህብረተሰቡም ራሱን ከተመሳሳይ የትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶችን ሊጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም