ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ ጋር ተወያዩ
የካቲት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
በወቅቱም ምክትል ዋና ጸሀፊዋ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጫናዎችን ውስጥ እያለፈ እንኳ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ በመመልከት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ያለውን ግንኙነት ገንቢ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
አክለውም በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ለመታደም መምጣታቸው በሀገሪቱ የአማራ፣ ሶማሌና ትግራይ ክልሎች ጉብኝት በማድረግ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በጉብኝታቸው በአካባቢዎቹ በተከሰቱ ግጭቶች የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን የጉዳት ደረጃ ለመገንዘብ መቻላቸውንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የተጀመሩ ጥረቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ የጠቆሙት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፣ ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎችም የመልሶ ግንባታ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል ምክትል ዋና ጸሐፊዋ እና ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል።
አያያዘውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ያለሙ ተከታታይ ስብሰባዎችን ማካሄዱ አግባብነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰላምን የማደፍረስ ተግባራትን እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደረግበትን ጫና በመቋቋም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን ለምክትል ዋና ጸሃፊዋ አስረድተዋቸዋል።
ሰሞኑን የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁም በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉ፣ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማከናወኑ፣ ከማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት መታቀቡ እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።
በህወሓት የሽብር ቡድን በኩል ግን መጀመሪያውንም በሀገሪቱ አጠቃላይ የሰላም መደፍረስ እንዲኖር አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ገልጸው፤ አሁንም በሚያደርገው ትንኮሳ የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዳይሆን ሆን ብሎ የማወክ ተግባሩን እንደቀጠለበት ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ እንዲሁም በተካሄዱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ህዝብ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሻ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት በየብስም ሆነ በአየር ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን በመደገፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
መንግስት ከተለያዩ አካላት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ተጨባጭ እውነታ የማስረዳት ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ለምክትል ዋና ጸሐፊዋ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።