ቀጥታ፡

ቤተ-ክርስቲያኗ በአውሮፕላን አደጋው የሰዎች ህይወት በማለፉ ሀዘኗን ገለጸች

አዲስ አበባ ነሀሴ 25/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በመከላከያ ሠራዊት አውሮፕላን በደረሰው አደጋ የሰዎች ህይወት በማለፉ የተሰማትን ሀዘን ገለጸች። የቤተ-ክርስቲያኒቱ ፓትሪያርክ አባ ማትያስ ቀዳማዊ እንዳሉት በተከሰተው ድንገተኛ አደጋ ቤተ-ክርስቲያኗ አዝናለች። "የልጆቻችን ኅልፈተ-ህይወት የሟቾቹ ቤተሰቦች ጉዳት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ በመሆኑ ሀዘኑ የጋራችን ነው" ብለዋል። በመሆኑም ለሟቾች የሰላም እረፍትን፤ ለሟች ቤተሰቦች፣ ለአየር ኃይል ሠራዊት አባላትና ለመከላከያ ሚኒስቴርም መጽናናትን ተመኝተዋል። በትናንትናው ዕለት ንብረትነቱ የመከላከያ ሠራዊት የሆነ አውሮፕላን ከድሬዳዋ ወደ ቢሾፍቱ 17 ሰዎችን አሳፍሮ በመብረር ላይ እያለ ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ናናዋ ቀበሌ አካባቢ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም