ከሰሜን ሸዋ ዞን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል የጓሮ አትክልት ምርት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ከሰሜን ሸዋ ዞን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል የጓሮ አትክልት ምርት ተገኝቷል
ደብረብርሀን የካቲት 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው በጋ ወቅት ከመጀመሪያ ዙር መስኖ ልማት ከሚጠበቀው የጓሮ አትክልት ምርት ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል መገኘቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ወይዘሮ አስካለ ይፍሩ ለኢዜአ እንደገለጹት የገጽና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም አርሶ አደሩ በመስኖ ልማት እንዲሳተፍ እየተደረገ ነው።
በዞኑ በበጋ ወቅት በመጀመሪያ ዙር መስኖ ስራ 91ሺህ 136 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 25ሺህ 303 ሄክታር መሬት በጓሮ አትክልት መልማቱን ተናግረዋል።
ከለማው መሬት ከሚጠበቀው አጠቃላይ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት ውስጥ እስካሁን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ካሮትና ጥቅል ጎመን መገኘቱን ገልጸዋል።
ምርቱ የተገኘው የመስኖ ልማቱ በተካሄደባቸው ኤፍራታ ግድም፣ አንፆኪያ ገምዛ፣ መርሀቤቴ፣ እንሳሮና ሌሎች ቆላማ ወረዳዎች መሆኑን አመልክተዋል።
ቀሪው ምርት ከማሳ ላይ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው በደጋማው አካባቢም በጦርነት የታጣን የሰብል ምርት ለማካካስ የመስኖ ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል ።
በበጀት አመቱ በበጋ መስኖ ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ቡድን መሪዋ አስታውቀዋል ።
በልማቱ ተሳታፊዎች መካከል የቀወት ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ታደሰ ዓየለ የውሀ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ያለሙትን ቀይ ሽንኩርት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
"የዘራሁትን የቆላ ስንዴም እየተንከባከብኩ ነው" ብለዋል።
"በሸዋሮቢት አካባቢ የለማ ቀይ ሽንኩርት በመድረሱ በኩንታል 1ሺህ 400 ብር ሂሳብ ገዝቼ እየሸጥኩ ነው" ያለው ደግሞ በደብረብርሀን ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ የተሰማራው ወጣት በላቸው ይርጉ ነው።
"አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 20 ብር ሂሳብ እየሸጠ መሆኑን ይገልጻል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከበጋ መስኖ ልማት 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱ ታውቋል ።