የሶማሌ ክልል ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሶማሌ ክልል ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል
አዲስ አበባ የካቲት 01/2014(ኢዜአ) የሶማሌ ክልል ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
ከዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከተከሰተው ድርቅ ገፈት ቀማሾች መካከል አርብቶ አደሩ የሶማሌ ማህበረሰብ በጉልህ ይጠቀሳል።
በዘንድሮው ድርቅ በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች የሚገኙ 88 ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ አርብቶ አደር የሆነውን የክልሉን ህዝብ ለከፍተኛ ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ ዳርጎታል።
ለድርቅ የተጋለጠው ሶማሌ ክልል ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌና ዳዋን የመሳሰሉ ዓመቱን ሙሉ ወራጅ ወንዞች ታድሎ ለምን ውሃ ይጠማል? የቁም እንስሳቱስ በግጦሽ እጦት ለምን ተንከራተቱ? የሚለው የብዙሃኑ ጥያቄ ነው።
በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ የሱፍ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ በየአሥር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ላይ የመከሰት ዕድሉ ወደ ሦስት ዓመት ዝቅ ብሏል።
በመሆኑም የክልሉ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከልም የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ አሰባስቦ መጠቀም አንዱ መሆኑን አቶ መሀመድ ጠቅሰዋል።
በክልሉ የውሃ ሃብትን ገድቦ ለመስኖ ማዋል ድርቅን መቋቋም የሚችል ህብረተሰብ ለመፍጠር ፕሮጀክቶች መነደፋቸውን ገልፀው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር በዘላቂ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሰሩ ከ200 በላይ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችም ዘንድሮ የተከተሰውን ድርቅ ለመቋቋም አጋዥ መሆናቸውን ለማሳያነት አንስተዋል።
ወራጅ ወንዞችን በመገደብም ሆነ የዝናብ ውሃን በማቆር በክልሉ በሚሰሩ ሥራዎች የመስኖ ግድቦች ለእንስሳት መኖ በማልማትና ወደ እርሻም በማስገባት ትኩረት ስለመደረጉ አንስተዋል።
እነዚህ የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም የሚሰሩ ዘላቂ ልማቶች ድርቅን ከመቋቋም ባለፈ የአርብቶ አደሩን ሕይወት ወደ ከፊል አርብቶ አደርነትና አርሶ አደርነት በመለወጥ የኑሮ ዘይቤውን የመለወጥ አቅም እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል በህወሓት የ27 ዓመታት አገዛዝ በመሰረተ ልማት ሆነ ተብሎ ወደኋላ እንዲቀር መደረጉን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ባለፈ ወደ ልማት ገብቷል ብለዋል።
በመንገድ፣ በመብራት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴሌኮምና በሌሎች መሰረተ ልማት ዘርፎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ክልሉ ለድርቅ ተጋላጭ ሆኖ ጉዳትን ያስተናገደው በእንስሳት ላይ ብቻ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ላይ በመንጠልጠሉ በመሆኑ የህብረተሰቡን የገቢ አማራጭ ማስፋት አብይ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ሰፊ መልክዓ ምድር የሚያካልል እና ከውጭ አገራት ጋር የሚካለልባቸው ሰፊ ድንበሮች እንዳሉት ጠቅሰው የገበያ ትስስር መፍጠርም ሌላው አማራጭ እንደሆነ አንስተዋል።
መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በመስኖ ልማትና መሰል የኢኮኖሚ አማራጮችን በማስፋት ከራሱ አልፎ ሌሎችን መጋቢ ክልል ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኑሮ ዘይቤውን በማስፋት ድርቅን ጨምሮ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የሚቋቋም አካባቢ ማድረግ የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት ሆኗል ነው ያሉት።