ቀጥታ፡

አገር አቀፉ የባህል ስፖርቶች ውድድር የፊታችን እሁድ በደብረ ብርሃን ከተማ ይጀመራል

አዲስ አበባ የካቲት 01/2014(ኢዜአ) አገር አቀፉ የባህል ስፖርቶች ውድድር የፊታችን እሁድ በደብረ ብርሃን ከተማ መካሄድ የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ሰለሞን አስፋው እንደገለጹት 19ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 15ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ከየካቲት 6 እስከ 13 ቀን 2014 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ ይካሄዳል።

በውድድሩ ከትግራይ በስተቀር ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሳተፉ ገልጸው ውድድሩ የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ ይካሄዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ባህሎች በመጤ ባህሎች እንዳይበረዙና ባህላዊ እሴቶቻችንን ለማጎልበት ውድድሩ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

የፌደሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ በላይነህ ሃይሌ፤ እንዳሉት እንደ አገር እስካሁን 293 የባህል ስፖርቶች ህግና ደንብ አልወጣላቸውም።

ከባህል ስፖርቶች መካከል 11 የባህል ስፖርት አይነቶች ህግና ደንብ የወጣላቸው መሆኑን ጠቅሰው ዘንድሮ በ10 የባህል የስፖርት አይነቶች ወድድር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በአገር አቀፉ የባህል ስፖርቶች ውድድር ከ900 በላይ ስፖርተኞች  እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም