ቀጥታ፡

ብሔራዊ መግባባትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የድርሻችንን እንወጣለን-በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

ሆሳዕና፤ የካቲት 1/2014 (ኢዜአ)፡ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚሰማሩበት አከባቢ ብሔራዊ መግባባትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት መርሐ ግብር ተመራቂ ወጣቶች ገለጹ።
ከተመራቂ ወጣቶች መካከል ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የዩ ወረዳ በመምጣት በዋቸሞ ዩንቨርስቲ ስልጠናውን ተከታትሎ የተመረቀው ወጣት አቤኔዘር ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ካለምንም የተለየ ጥቅም ለሌሎች መኖርና ሌሎችን ማገልገል በመሆኑ የሚሰጠው መንፈሳዊ እርካታ ወደር የለውም ።

ለስልጠና በቆየባቸው ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቱባ ባህሎች ለአዕምሮ ብስለት፣ ለጠንካራ የስራ ባህልና ለሀገር ፍቅር ያላቸውን አስተዋጽኦ መገንዘብ መቻሉን ተናግሯል።

ማህበረሰቡን በበጎ ፈቃድ ለማገልገል ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ገንቢ ባህሎችና እሴቶችን በማጉላት  ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጧል ።

ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው የዘረኝነትና ጎጠኝነት አተያይ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እንዲመለከት ማድረጉን አስታውሶ፤ "አስተሳሰቡን በማምከን ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረባት ሀገር እንድትገነባ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል" ብሏል።

ከሰሜን ጎንደር ዞን ጎሀላ ወረዳ ስልጠናውን የተከታተለችው ወጣት ህይወት በሪሁን በበኩሏ "ቀደምት አባቶች በብሔርና በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ሳይከፋፈሉ በአንድነት ፀንተው በመቆማቸው ነፃነቷ የተከበረ  ሀገር አስረክበውናል" ብላለች።

በሀገር ጉዳይ ለመጣ ጠላት  የማይንበረከክ መሆኑን በታሪክ ያስመሰከረው የኢትዮጵያ ህዝብ  ህወሓት የለኮሰውን ጦርነት ለማምከን ቀፎው እንደ ተነካ ንብ በአንድነት ግንባር ድረስ በመትመም በተግባር ማረጋገጡን ጠቁማለች።

ልዩነቶችን በማቻቻል የሀገር ህልውናን አሳልፈው ለመስጠት የሚጥሩ የውስጥ ባንዳዎችን በማሳፈር ይበልጥ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክታለች።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ማህበረሰቡ በምትቀላቀልበት ወቅት ዘላቂና ጠንካራ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት  የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝ ገልጻለች።

''ጠንካራ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት ያሉንን የሰላም እሴቶችን ማጉላት ቀዳሚ አማራጭ ነው'' ያለው ደግሞ ከአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በመምጣት ስልጠናውን የተከታተለው ወጣት መልካሙ ሀሰን ነው።

የልዩነት ሴራው  ሀገርና ህዝብን መጉዳቱን የጠቀሰው ወጣት መልካሙ፤ "ይህንን በመረዳት አንድነታችንን አጠናክረን የኢትዮጵያን ህልውና የምናስቀጥልበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን" ብሏል።

''ለሰላምና ለአንድነት መሪ ተዋናይ ልንሆን የሚገባን  እኛ ወጣቶች ነን'' ያለው  ወጣቱ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚሰማራበት አካባቢ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚወጣ አመላክቷል።

የሰላም ሚኒስቴር ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለተከታታይ  ለ45 ቀናት በብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት መርሐ ግብር አሰልጥኖ ያለፈው እሑድ ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ማስመረቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም