የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን ራዕይ ሰንቆ መስራት አለበት-ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት

አዲስ አበባ ነሀሴ 25/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን ራዕይ ሰንቆ መስራት እንዳለበት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ። ኤጀንሲው በከተማ ደረጃ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ላይ የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች እውቅና ሰጥቷል። የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እውቅና በተሰጠበት ወቅት እንዳሉት፤ ኤጀንሲው አሁን ያገኘው ውጤት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ራዕይ ሰንቆ መስራት ይኖርበታል። ''የከተማችን ነዋሪ የሚፈልገው አገልግሎት እጅግ በጣም የዘመነና ያደጉ አገሮች በደረሱበት ደረጃ ሊለካና ሊመዘን የሚችል በመሆኑ በዚሁ ልክ የሚለካ አገልግሎት ከዚህ ተቋም ይጠበቃል'' ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ኤጀንሲው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከተማው እየመጣ ያለውን የህብረተሰብ ፍላጎት ለማስተናገድ ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ዳግማዊት መልካም አስተዳደር ማስፈን ላይ የመሥራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ በ2010 ዓ.ም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ላይ ስኬታማ ሥራ በመስራቱና የላቀ ውጤት በማስመዝገቡ በዘርፉ በአገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ማድረጉም ተገልጿል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ተሾመ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ከፍተኛ ሥራ አከኗውኗል። ምዝገባው ለሕግ፣ ለስታቲክስና አስተዳደር ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸዋል። ኤጀንሲው በ2009 ዓም በአሻራ በመታገዝ በከተማ ደረጃ  ከ106 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሞት፣ የልደት፣ የጋብቻና ፍቺ ምዝገባ ማከናወኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በ2010 ዓ.ም ደግሞ ከ300 ሺህ ያላነሱ ዜጎች እንደተመዘገቡ አመልክተዋል። እንደ አቶ አስናቀ ገለጻ፤ በተጠናቀቀው ዓመት 900 ሺህ ለሚሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች የመታወቂያ ማደስ፣ አዲስ መታወቂያ ማውጣትና እርማትና ግልባጭ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ተሰጥተዋል። ''በቀጣይ አገልግሎቱን ለማዘመን የመታወቂያ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዲጂታል የማድረጉ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል። እውቅና ከተሰጣቸው መካከል የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ዋሳኝ ኩነት ምዝገባ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ በየነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በወረዳው ለፈጻሚውና ለተገልጋዮች የተፈጠረው ግንዛቤ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን አግዟል። ''የእቅዳችንን 90 በመቶ ማሳካት ችለናል'' ያሉት ሥራ አስኪያጁ ይህም ለእውቅና እንዳበቃቸው ተናግረዋል። የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ የኑስ ሽንብር በበኩቸው በዓመቱ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ጠንካራ ዝግጅት በመደረጉ ውጤታማ ተግባር እንደረከናወነ አብራርተዋል። ለአብነትም በ90 ቀናት ውስጥ ከ1ሺህ 500 በላይ ህጻናት ወቅታዊ ምዝገባ እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው በክፍለ ከተማ ደረጃ በአጠቃላይ ኩነት ምዝገባ ከ180 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አገግልግሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል። በዕለቱ ከጤና ተቋማት መካከል የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ባስመዘገበው አፈጻጸም ተሸላሚ ሆኗል። ነሃሴ 24 ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም