በአፍሪካ ድህነትን በዘላቂነት ለመቀነስ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ድህነትን በዘላቂነት ለመቀነስ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2014 በአፍሪካ ድህነትን በዘላቂነት ለመቀነስ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ ከባቢ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ከሚሽነሯ አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአህጉሪቷ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ስራ አጥ ናቸው፡፡
ይህም የአፍሪካ ልማትን በማፋጠን የአህጉሪቷን ህዝቦች ኑሮ ለማሻሻል እየተከናወነ ያለው ጥረት ላይ እክል መፍጠሩን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የህብረቱ አባል አገራት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ህብረቱ ለድህነት ቅነሳ አጋዥ የሆኑ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፋይናንስ በማፈላለግ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፤ ወጣቶችን በማብቃት አምራች ኃይል ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት የሆነውና 70 በመቶ የሚሆነው የአህጉሪቷ ህዝብ የሚተዳደርበት ግብርና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለውም አመላክተዋል።
ህብረቱ በግብርና ላይ የተንጠለጠለውን የአፍሪካን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።
በዚህም ወጣቶች ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን በማምረት ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚችሉም ነው ያነሱት፡፡
ወጣቶች ከስራ ጠባቂነት ይልቅ የስራ ፈጣሪነት አስተሳሰብን በመያዝ የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መትጋት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች በበኩላቸው፤ አፍሪካዊያን ጠንካራ የስራ ባህልን ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከሳህራዊ አረብ ሪፐብሊክ የመጡት አምባሳደር ሞሃመድ የስሊም፤ አፍሪካ ያላትን የግብርና አቅም ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ለስራ እድል ፈጠራና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከታንዛኒያ የመጡት ታማቤሌ ሲምባ በበኩላቸው በአፍሪካ ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚቻለው ጠንካራ የስራ ባህልን በማጎልበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ጠንካራ የስራ ባህልን ከማጎልበት በተጨማሪ በአፍሪካዊያን መካከል ትብብር እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡