በግንባታና እድሳት ላይ ያሉ ስታዲየሞችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግንባታና እድሳት ላይ ያሉ ስታዲየሞችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ጥር 30/2014 በግንባታና እድሳት ላይ ያሉ ስታዲየሞች ዓለም አቀፍ ውድድር ማስተናገድ የሚችሉበትን መስፈርት አሟልተው በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ለበርካታ ዓመታት አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያስተናግድ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም ካፍ ያስቀመጠውን ደረጃ ማሟላት ባለመቻሉ ከሶስት ዓመት በፊት መታገዱ ይታወቃል።
የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍ ከታገደ በኋላ የባህር ዳር ስታዲየም የተቀመጡ መመዘኛ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ባያሟላም በቀነ-ገደብ ውድድሮችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
ነገር ግን የአፍሪካ እግርኳስ ፌዴሬሽን "በተቀመጠው ቀነ-ገደብ መስፈርቱን አላሟላም" በሚል ምክንያት የባህር ዳር ስታዲየምን ከጥቅምት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን እንዳያስተናግድ አግዶታል፡፡
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ከአገር ውጭ እንዲያካሂድ ሆኗል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ በርካታ ስታዲየሞች እየተገነቡ ቢሆንም በፋይናንስ እጥረትና ሌሎች ተግዳሮቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡
በዚህም ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖቻችን በሌላ አገር እንዲጫወቱ መገደዳቸውን አስታውሰዋል።
ይህም ከደጋፊዎች እርቀው እንዲጫወቱ በማድረግ በውጤቱ ላይ ተጽእኖ ከማሳደሩ ባለፈ ኢትዮጵያ የተጋጣሚ አገራትን ወጪ እንድትሸፍን የምትገደድበት ሁኔታ ፈጥሯል።
በፌደራል መንግስት ወጪ እየተከናወነ ያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትና የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በመንግስት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየምን በጎበኙበት ወቅት ለግንባታው የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ችግር በአስቸኳይ እንዲፈታና ስራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ መመሪያ መስጠታቸውንም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የአደይ አበባ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታና የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትን በቶሎ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
34ኛው የአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ የሚጀመረበት ጊዜ ቅርብ በመሆኑ ስታዲየሞችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባም አንስተዋል።
በክልሎች በኩል እየተሰሩ ያሉ ስታዲየሞች ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ የባለድርሻ አካላት የጋራ መድረክ በቅርብ ጊዜ እንደሚካሄድ ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ገልጸዋል።