"ኢትዮጵያ የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ መልኩ ማከናወኗ ለዓለም ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው" - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያ የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ መልኩ ማከናወኗ ለዓለም ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው"
ጥር 30/2014/ኢዜአ/ "ኢትዮጵያ 35ኛውን የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ መልኩ ማከናወኗ ለዓለም ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው" ስትል ሱዳናዊቷ የአል-አረቢያ ሚዲያ ዘጋቢ ሩፋይዳ ያሲን ገለጸች።
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ የተለያዩ የማሰናከያ ጥረቶች ቢደረጉም በጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ጉባኤው በተሳካ መልኩ ተከናውኗል።
ኢትዮጵያ እንግዶቿን በጥሩ መስተንግዶ ተቀብላ በቆይታቸው እንዲደሰቱ በማድረግ ጉባኤው ሲጠናቀቅም በክብር ሸኝታለች።
በመሆኑም ኢትዮጵያ 35ኛውን የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ መልኩ ማከናወኗ ለዓለም ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ለዘገባ አዲስ አበባ የተገኘችው ሱዳናዊቷ የአል-አረቢያ ሚዲያ ዘጋቢ ሩፋይዳ ያሲን ገልፃለች።
''በእርግጥ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሳስብ በአንዳንድ ሚዲያዎች በሚራገበው የተጋነነ ዘገባ ፈርቼ ነበር'' የምትለው ጋዜጠኛዋ አዲስ አበባ ስትደርስ ፍፁም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልክቻለሁ ብላለች።
አዲስ አበባ አምራና ተውባ በጥሩ መስተንግዶ ተቀብላን አስደሳችና የተሳካ ቆይታ አድርገናል ነው ያለችው።
ኢትዮጵያ አስደናቂና ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አገር መሆኗን የጠቀሰችው ጋዜጠኛዋ "ደጋግመው ለመምጣት የሚያስቧትና የሚመኟት አገር" ስትል ገልፃለች።
የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ ሰላም በመሆኑ ለሰላም፣ ልማትና አብሮነት አፍሪካዊያን በጋራ መቆም አለብን ብላለች።
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ሚዛናዊ ዘገባዎችን በማቅረብ እውነትን ብቻ መሰረት አድርገው መዘገብ አለባቸው ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤"የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማበት፣ የፓን አፍሪካዊነት ድምጽ የሚንጸባረቅበት የጋራ አህጉራዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።