ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከ464 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን የመምህራን መኖሪያ አስመረቀ

116

ጥር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከ464 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የገንዘብ ወጪ ያስገነባውን ዘመናዊ የመምህራን መኖሪያ ህንጻ በዛሬው ዕለት አስመረቀ ።

በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሀላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዩኒቨርሲቲው የመምህራን መኖሪያ ህንጻ መገንባቱ የመኖሪያ ቤት ችግር በማቃለል መምህራን ተረጋግተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ያስችላል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል የመምህራን መኖሪያ ህንጻ ከ1 ሺህ 700 በላይ ካሬ መሬት ላይ ያረፈና አራት ብሎኮች እንዳሉት ገልጸው፤ 72 ባለ ሁለት መኝታ፣ 120 ባለ አንድ መኝታ እንዲሁም 60 ስቱዲዮዎች ያካተቱና 252 አባወራዎችን የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ግንባታው መምህራንን በአንድ አካባቢ ሰብስቦ የያዘ መሆኑ አብሮነትና የመተሳሰብ ባህልን ከመገንባት አንጻር ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

መምህራኑ ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ ይገጥማቸው የነበረውን ችግር እንደሚፈታ የገለጹት ዶክተር ፋሪስ፤ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በመንደሩ የሚኖሩ የመምህራን ልጆች ትምህርታቸውን ሳይርቁ  እንዲማሩ ለማስቻል የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን ጠቁመዋል።

የመምህራን መኖሪያው የራሱ የሆነ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርሜርና ከከርሰ ምድር የጥልቅ ጉድጓፍ ውሃ ያለው በመሆኑ ለኑሮ ምቹ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ህንጻው ለነዋሪዎች አስፈላጊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አሟልቶ የያዘ ሆኖ መገንባቱን አስታውቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓት በመገኘት የመኖሪያ ቤት ቁልፍ የተረከቡት መምህር ተሾመ ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ችግር አይቶ የመኖሪያ ህንጻ አስገንብቶ ቁልፍ ማስረከቡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም