የምክትል ዋና ፀሐፊዋ ጉብኝት አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ያደረሰውን ጉዳት በጥቂቱ ለማሳየት አስችሏል-ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ - ኢዜአ አማርኛ
የምክትል ዋና ፀሐፊዋ ጉብኝት አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ያደረሰውን ጉዳት በጥቂቱ ለማሳየት አስችሏል-ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ
ደሴ ጥር 29/2014(ኢዜአ)የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በአማራ ክልል ያደረጉት ጉብኝት አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ጉዳት በጥቂቱ ለማሳየት እንዳስቻለ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር ገለፁ፡፡
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በደቡብ ወሎ ዞን በኮምቦልቻ ከተማ በሽብር ቡድኑ ጥቃት ከደረሰባቸው ወገኖች ጋር የተወያዩ ሲሆን በአሸባሪው ቡድን የወደመውንና የጅምላ መቃብር የተፈጸመበትን የኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ኮሌጅ ተመልክተዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ወደ ከተማዋ ያቀኑት አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በአካል ተገኝተው እውነቱን ለማወቅ ነው፡፡
ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድ ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን፣ ህጻናትና አረጋዊያንን ሳይቀር መድፈሩን ያስታወሱት ዶክተር ጌታቸው ንብረት መዝረፉንና ያልቻለውን ማውደሙን አስረድተዋል፡፡
ለምክትል ዋና ፀሐፊዋ ከደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት መካከል የጥፋቱን ማሳያዎች እንደቀረቡላቸው ገልጸዋል፡፡
''ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ጉዳቱን በቦታው ተገኝተው መመልክታቸው ድርጅቱ ከአድልኦ ተቆጥቦ ከፍትህና ከእውነት ጎን እንዲቆም ዕድል ይፈጥራል'' ብለዋል፡፡
"በተለይም በቡድኑ ቤተሰቦቻቸው ከተገደሉባቸው፣ አካላቸው ከጎደለ፣ ከተደፈሩና ከተሰቃዩ ሴቶች፣ ህጻናትና ሌሎች አካላት ጋር ፊት ለፊት እንዲወያዩና የጥቃቱን አስከፊነት እንዲያስረዱ መደረጉ ድርጅቱ በተለመደና በተሳሳተ መረጃ እንዳይወዛገብ ያደርጋል" ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሰላም ከምንም በላይ ቢፈልጉም፤ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ መምጣት ስለማይችል ተገደው ወደ ጦርነት መግባታቸውን ለምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ማስረዳታቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡
"አሸባሪው ቡድን በቀጣይ ዘላቂ ሰላምና አንድነት የሚፈልግ ከሆነም፤ ቢያንስ ወረራ ከፈጸመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ተጠራርጎ መውጣት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ አሚና መሐመድ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይትና ምልክታ ውጤታማ እንደሚሆንም ዶክተር ጌታቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ አሁንም ወጣቶችን በማሰልጠን በተለያዩ አካባቢዎች ትንኮሳ በማድረግና ዳግም ጥፋት ለማድረስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው "የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን በማስጠበቅ ጠላቶቹን መመከትና ሉዓላዊነቱን ማስጠበቅ ይገባዋል" ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው አሸባሪው ቡድኑ ካደረሰው ሁለንተዊ ጥፋት ባለፈ የእምነት ተቋማትን ጭምር ማውደሙንና ማርከሱን ለምክትል ዋና ፀሐፊዋ እንዳስረዷቸው ተናግረዋል፡፡
የዓለም ህዝብም እውነቱን ተገንዝቦ ለእውነትና ለፍትህ መታገል እንጂ፤ አሸባሪው ቡድን በሚያቀነባብረው የሐሰት ወሬ መደናገርና ፍርድ ማዛባት የለበትም" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ምክትል ዋና ጸሀፊዋ ይህንኑ እውነታ እንዲገነዘቡት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱና በጉብኝቱ ላይ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡