ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ይደግፋል

ጥር 29/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር እንደሚደግፍ የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፤ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽነሩ አምባሳደር ባንኮሊ አዲኦይ በሰጡት መግለጫ  የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር አፍሪካዊ በሆነ መፍትሔ ለመፍታት ሲያደርጋቸው የነበሩ ጥረቶችን ዘርዝረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት አካታች ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀው፤ የአፍሪካ ህብረት ለምክክሩ ስኬት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ህብረቱ ምክክር ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በሃብት፤ በሙያና በሌሎች ተመሳሳይ መስኮች እንደሚደግፍም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በግጭቱ ሳቢያ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማረጋገጣቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቷ በወታደራዊ ኃይል መንግስት ለመገልበጥ የሚደረግ ሙከራን እንደማይታገስ ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡

በ35ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጉዳዩን በሚመለከት ሰፊ ውይይት ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ጉባኤው ህብረቱ ቀደም ሲል የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን ለመፍጠር የያዘውን አጀንዳ  እውን ለማድረግ በሚያስችሉ የቀጣይ ስራዎች ላይ መምከሩንም ተናግረዋል፡፡

ከሚሽነሩ በመግለጫቸው ሽብርተኝነት እና የፖለቲካ ሽግግርን እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአህጉሪቷ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ ያስከተለውን ተጽእኖ በሚመለከትም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም