ባንኩ በሐረር ከተማ በ8 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው ጤና ጣቢያ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በሐረር ከተማ በ8 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው ጤና ጣቢያ ተመረቀ
ሐረር ጥር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረገው የ8 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ በሐረር ከተማ የተገነባው የሸንኮር ወረዳ ጤና ጣቢያ ዛሬ ተመረቀ።
ለጤና ጣቢያው ከመንግሥት በተመደበ ከ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሕክምና ቁሳቁስ፣መድሃኒትና ሌሎች ግብአቶች የተሟላለት መሆኑ ተመልክቷል።
ጤና ጣቢያውን የመረቁት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሐመድ ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ጥራትና ተደራሽነትን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ ነው።
ጤና ጣቢያው የአካባቢው ነዋሪዎች ሲያነሱት ለነበረው ችግር ምላሽ እንደሰጠና የሕክምና መሳሪያዎች እንደተሟሉለት አቶ ኦርዲን ተናግረዋል።
የግንባታ ወጪውን ለሸፈነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት ጤና ጣቢያውን ለእናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ በበኩላቸው ባንኩ ካከናወነው ግንባታ በተጨማሪ የክልሉ መንግሥት ለጤና ጣቢያው ከ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሕክምና ቁሳቁስ፣ መድሃኒትና ሌሎች ግብአቶች ማሟላቱን ተናግረዋል።
ጤና ጣቢያው በተለይ በእናቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ጤና ባለሙያዎች የተመደቡለት መሆኑን ጠቁመው የቀዶ ጥገና፣ የአልትራ ሳውንድ፣ የላብራቶሪ፣ የፋርማሲ፣ የህክምና ቁሳቁስ መሟላታቸውን ተናግረዋል።
በሸንኮር ወረዳ የተገነባው ጤና ጣቢያ በአቅራቢያው ለሚገኙት ለአሚር ኑርና ለአቦከር ወረዳ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ "ጤና ጣቢያው የህክምና አገልግሎት በአቅራቢያችን ለማግኘት ያስችለናል" ብለዋል።