የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ ተዘጋጅቷል
ሰመራ ነሀሴ 25/2010 የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በ2011 የትምህር ዘመን የተማሪዎች የቅበላ አቅሙን ከ3ሺ በላይ በመጨመር ለማሳደግ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርስቲው በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ስምንት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን እንደሚከፍትም ተመልክቷል፡፡ የተቋሙ አካዳሚክ ምክትል ፕሪዝዳንት ተወካይ አቶ መሃመድ የሱፍ እንደገለጹት ባለፉት አስር ዓመታት ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህንኑ ለማጠናከር በ2011 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርስቲው ስር በሚገኙ ሰባት ኮሌጆች 3ሺህ 10 ተማሪዎችን በተጨማሪ ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል፡፡ ከዝግጅቶቹ መካከል የተማሪዎች መማሪያና ማደሪያ ክፍሎች ማመቻቸት ፣ የቤተ ሙከራ ማደራጀትና የመምህራን ቅጥር ይገኙበታል፡፡ ዩኒቨርስቲው በተጨማሪ የሚቀበላቸውን ጨምሮ በመደበኛ የትምህርት መርሃ-ግብር የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ቁጥር ወደ 7ሺህ 500 እንደሚያሳደግ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ሌላ ዩኒቨርስቲው ከነበሩት 35 የትምህርት ክፍሎች በተጨማሪ በመጀመሪያ ዲግሪ አራት አዳዲስ የትምህርት መረሃ ግብሮችን ለመክፈት እየተሰናዳ መሆኑን አቶ መሃመድ አመልክተዋል፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ ከሚከፈቱት ውስጥ አርኪኦሎጂ፣ ውሃ ሃብት ልማት እና የመስኖ ምህንድስና ይገኙበታል፡፡ በሁለተኛ ዲግሪም አራት የትምህርት ክፍሎች በመክፈት ዩኒቨርስቲው በዚህ ደረጃው የሚሰጠው የትምህርት ክፍሎች ወደ አስር ይደርሳሉ ተብሏል፡፡ እንስሳት ጤና ፣ ሰብል ልማት ፣ ተፈጥሮ ሃብት ክብካቢና ልማት መስኮች በሁለተኛ ዲግሪ የሚከፈቱ የትምህር ክፍሎች ናቸው፡፡ አዳዲሰቹ የትምህርት ክፍሎች በ2011 የትምህርት ዘመን ለመጀመር የስርዓተ ትምህርት ቀረጻና ሌሎችንም ቅድመ ዝግጅቶች በመገባደድ ላይ እንሚገኝ ተመልክቷል፡፡ የሰመራ ዩኒቨርስቲ በ2000 ዓ.ም. ስራ ከጀመሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡