ቀጥታ፡

በሽብር ቡድኑ የወደመው ሐይቅ ቁጥር-2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በ10 ሚሊዮን ብር መልሶ ሊገነባ ነው

ደሴ፣ ጥር 28/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት የወደመው ሐይቅ ቁጥር-2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በ10 ሚሊዮን ብር መልሶ ለመገንባት ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

በሽብር ቡድኑ የወደመው የሐይቅ ቁጥር-2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መልሶ የሚገነባው በአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ እና በግሎባል አሊያንስ ትብብር እንደሆነ ተገልጿል።

ትምህርት ቤቱን መልሶ ለመገንባት የመሠረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የአማራ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ እና አርቲስት ታማኝ በየነ ናቸው።

የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ በሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር የፈጸመው ወረራ በመላ ኢትዮጵያዊያን ትግል ተቀልብሷል።

"ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ትምህርት ቤት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ገንብቶ በማጠናቀቅ መልሶ ለአገልግሎት ለማብቃት በቅንጅት እንሰራለን" ብለዋል።

አልማ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ መልኩ መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መላኩ፣ ሁሉም በሚችለው ማህበሩን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የግሎባል አሊያንስ መስራችና ኃላፊ አርቲስት ታማኝ በየነ እንደገለጸው፣ በአሸባሪ ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ኢትዮጵያዊ ጀግንነትን ዳግም ማረጋገጥ ይገባል።

በዚህም ግሎባል አልያንስ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በአማራ እና በአፋር የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በቅንጅት መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

የሐይቅ ቁጥር-2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን በ10 ሚሊዮን ብር መልሶ ለመገንባት  የመሠረተ ድንጋይ መቀመጡንም አስረድቷል።

ትምህርት ቤቱን ለማስገንባት ከአማራ ልማት ማህበር ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም  አርቲስት ታማኝ ገልጿል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አቢ በበኩላቸው፣ "በክልሉ በሽብር ቡድኑ ጉዳት ከደረሰባቸው 4 ሺህ 107 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 25ቱ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል" ብለዋል።

ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በመልሶ ማቋቋም ስራው ዳያስፖራው፣ ክልሎችና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በግሎባል አሊያንስና በአልማ ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ትምህርት ቤት አራት ሕንጻዎች እንደሚገነቡለት የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ናቸው።

በትምህርት ቤቱ ከ1 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ጠቁመው ግንባታውን በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ዞኑ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም