የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው-- የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው-- የጤና ሚኒስቴር
አዳማ፣ ጥር 28/2014 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ክትባቱን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ በሚቻልበት ሂደት ላይ ከክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ከተውጣጡ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ጋር በአዳማ እየመከረ ነው።
በጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የኮሮና ክትባት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ለማ እንደገለጹት ክትባቱን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ።
አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በመሆናቸው በሽታውን ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት መውሰድ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በተለይ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ኮሮናን ለመከላከል በሚሰጠው ክትባት ላይ የጋራ ግንዛቤ ይዘው ለእቅዱ ውጤታማነት ጥረት እንዲያደርጉ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
"አካል ጉዳተኞች በመጀመሪያ ደረጃ ክትባቱን ማግኘት ካለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ናቸው" ያሉት አስተባባሪው፤ ለተግባራዊነቱ ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት ጥረት ማድረግ ማስፈለጉን ጠቁመዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መከተባቸውን አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው "አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት አግኝተው ክትባቱ ተደራሽ እንዲሆን ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ ነው "ብለዋል።
"በሚቀጥለው ወር ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴርና ከክልሎች የጤና ቢሮዎች ጋር በትብብር እየሰራን ነው" ሲሉም አመልክተዋል።
በየደረጃው ያሉ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እንዲያስተባብሩና በቅንጅት የንቅናቄው አካል እንዲሆኑ አስገንዝበዋል።
አቶ አባይነህ አክለውም አካል ጉዳተኞች ክትባቱን በመከተብ እራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።