የህብረተሰቡን የጤና ችግር ከመሰረቱ መፍታት የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ ማተኮር ይገባል -ጤና ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰቡን የጤና ችግር ከመሰረቱ መፍታት የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ ማተኮር ይገባል -ጤና ሚኒስትር
አዳማ፣ ጥር 28/2014 (ኢዜአ) የህብረተሰቡን የጤና ችግር ከመሰረቱ መፍታት የሚችል ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስገነዘቡ።
የአዳማ ጄኔራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በጤና ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ከ200 በላይ የህክምና ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለፁት የህብረተሰቡን የጤና ችግር ከመሰረቱ መፍታት የሚችል ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ ነው።
ከህክምና አገልግሎት በተጨማሪ በሰው ሃይል ልማት ላይ በትኩረት በመስራት በበቂ ደረጃ ተደራሽ ያልሆነውን የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ከማረጋገጥ ባለፈ በህብረተሰቡ ውስጥ የጤና ችግሮችን በጥናትና ምርምር ጭምር በመለየት መፍትሄ ማመንጨት የሚችል የዘርፉ ሙያተኛ ማፍራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል ።
"የአዳማ ጄኔራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በጤና ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሀይል የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል ።
የሚዲካል ኮሌጁ ዲን አቶ ዲሪባ ደገፋ በበኩላቸው ኮሌጁ ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተጋ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሌጁ በዛሬው እለት ለ5ኛ ጊዜ በራዲዮሎጅ፣ በአዋላጅ ነርስ፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና ጨምሮ በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ200 በላይ ባለሞያዎች ማስመረቁን አስታውቀዋል ።