ቀጥታ፡

በአፍሪካ የሚደረግን ማንኛውም ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) "በአፍሪካ የሚደረግን ማንኛውም ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል" ሲሉ ተሰናባቹ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ሺሲኬዲ ጥሪ አቀረቡ።

የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በመሆን ለአንድ ዓመት የመሩት የዲሞክራቲክ ረፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሲኬዲ ሃላፊነታቸውን የወቅቱ ሊቀመንበር ሆነው ለተመረጡት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳነት ማኪ ሳል አስረክበዋል።ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሲኬዲ በስንብት ንግግራቸው ህብረቱን በሊቀመንበርነት በመሩበት ቆይታቸው የነበራቸውን ክንውን ጠቅሰዋል።

ለፓን አፍሪካ ባሕል ህዳሴ፣ በሴቶች ተሳትፎና እኩልነት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በአፍርካ ነጻ ንግድ ቀጣና፣ በአየር ንብርት ለውጥ እና መሰል ጉዳዮች በርካታ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

በአባል አገራቱ የሚደረጉ ያልተገቡ ውጫዊ ጣልቃ ገብነቶች ለመመከት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።በአባል አገራት መካከል የጋራ ልማት እንጂ ግጭቶች እንዳይኖሩ የተከናወኑ ተግባራትንም አንስተዋል።

ለአብነትም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት የሶስትዮሽ ድርድር እንዲያደርጉ ህብረቱ ጥረት ስለማድረጉ ጠቅሰዋል።

አባል አገራቱ መቻቻል እና የጋራ ልማት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ፕሬዝዳንት ሺሲኬዲ፤ በአፍሪካ የሚደረግን ማንኛውም ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።

ከሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም የመንግስት ለውጥ የሕብረቱ ድንጋጌ እንዲያወግዘው ገልጸው፤ ዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርዓትን በአፍሪካ ማስፈን ይገባናል ሲሉም ጠይቀዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ እና አገራትን በሚያስተሳስሩ ኢኮኖሚዊ ትብብሮች ላይም ይብልጥ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

አገራቸው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ ለአፍሪካ አንድነት እና ዕድገት በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉም አረጋግጠዋል።በአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርንት ቆይታቸው ለተደረገላችው ትብብር አመስግነው፤ ለተተኪያቸው መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም