አፍሪካውያን ውስጣዊ ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት ይችላሉ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ውስጣዊ ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት ይችላሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28/ 2014(ኢዜአ) አፍሪካውያን ውስጣዊ ችግራቸውን በራሳቸው አቅም የመፍታት አቅም እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በህብረቱ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአፍሪካ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን፣ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና በሽታን ለመከላከል በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ አብሮነትና ትብብራችን ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ዘላቂ ልማት እንዲመጣ "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" መስጠት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
አፍሪካ ባለፉት ዓመታት በድርቅ፣ ኮቪድ-19፣ ጎርፍና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች መፈተኗን አስታውሰው ፈተናዎችን ለማለፍ አብሮነታችን ያስፈልጋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።
ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስጣዊ ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል አፍሪካዊያን ስላመኑን፣ ስለተረዱንና ላሳዩን አብሮነት ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በውስጥ ሃይሎች የገጠማትን ችግር በራሷ አቅም በመፍታት ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ጥረት እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ጉዳቱን ለመቀነስ የተለያዩ የሰላም አማራጮችን ተከትሎ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም መንግስት የሰላምና የውይይት መድረኮች እንዲኖሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።