የአለም የፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአለም የፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ነሃሴ 25/2010 የአለም የፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ በአፍሪካ ሕብረት እንደሚጀመር የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከነሀሴ 28 እስከ ጳጉሜ 2 ቀን 2010 ዓም የሚካሄደውን ልዩ ጉባኤ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው ላይ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መብራቱ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ የአለም የፖስታ ህብረት እአአ በ2016 በቱርክ ኢስታንቡል ባካሄደው ስብሰባ ከ118 ዓመታት በፊት እአአ በ1900 በስዊዘርላንድ የተካሄደው የህብረቱ ልዩ ጉባኤ ቀጣይ የሆነው ሁለተኛው ልዩ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፏል። በልዩ ጉባዔው የሕብረቱ ሪፎርም ጉዳዮች፣ የአባላቱ መዋጮ ሪፎርም፣ የተቀናጀ አገልግሎትና የክፍያ ሁኔታ እቅድ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በጉባኤው ከህብረቱ 192 አባል አገሮች የተውጣጡ 1 ሺህ 500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች የሚገኙ ሲሆን ዘርፉን የሚመሩ ሚኒስትሮች፣ የዓለም የፖስታ ህብረት ዳይሬክተር፣ አህጉራዊ ፖስታ አስተዳደር ሀላፊዎችና የአለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ይገኛሉ። የአለም ፖስታ ሕብረት ስትራቴጂ አተገባበርና የፖስታ አገልግሎት ዘርፍ ለአገሮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ተሳታፊዎች የሚያርፉባቸው 28 ሆቴሎች መዘጋጀታቸውንና የእንግዶቹ ደህንነት ለማስጠበቅም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆቱንም አንስተዋል። እንደ ዶክተር መብራቱ ገለጻ፤ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ አገሪቷ ከአፍሪካ ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻ መካከል መሆኗን ለማሳየት፣ ለገጽታ ግንባታና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የራሱ የሆነ አወንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በዘርፉ ስኬታማ የሆኑ ተሞክሮዎችን ለመቅሰምና በዘርፉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ተቋማት መካከል ለመሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።