ዳያስፖራው ህጋዊ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ ስርዓትን በመከተል ለኢትዮጵያ ልማት የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ህጋዊ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ ስርዓትን በመከተል ለኢትዮጵያ ልማት የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል
አዲስ አበባ ፣ ጥር 27/2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ህጋዊ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ ስርዓትን በመከተል ለኢትዮጵያ ልማት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የዳያስፖራ ማሕበረሰብ ተወካዮች ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ከተውጣጡ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላትና ተወካዮች ጋር ህጋዊ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ ስርዓትን ማጎልበት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
በመድረኩም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ባንኩ ያመቻቸውን የዳያስፖራ ሂሳብ ቁጥር አባል በመሆን የውጭ አገራት ገንዘቦችን በአገር ውስጥ እንዲቆጥቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጡሪ ጎሼ በዚህን ወቅት ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ያደረገውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል፡፡
የዳያስፖራውን ተሳትፎ በቋሚነት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ባንኩ ህጋዊ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ እንዲጎለብት ከመስራት ጀምሮ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ዳያስፖራው ራሱን እየጠቀመ አገሩን የሚያግዝበት የቁጠባና የድጋፍ አሰራሮችን መዘርጋቱንም ገልጸዋል፡፡
በአውሮፓ የዲፌንድ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ዘላለም ጌታሁን በበኩላቸው ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ጉልህ ሚና ማበርከት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ዳያስፖራው ህጋዊ የምንዛሪ ስርዓትን በመከተልና በአገር ውስጥ በተከፈቱ የዳያስፖራ አካውንቶች አባል ሆኖ በመቆጠብ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይችላል ነው ያሉት፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ጣሰው መላዕከህይወት በበኩላቸው ዳያስፖራው የውጭ አገር ገንዘቦችን በአገር ውስጥ ባንኮች በመቆጠብ ለኢትዮጵያ ልማት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ ኢንቨስትመንት አማራጮች መሳተፍ እንዳለበትም እንዲሁ፡፡