በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው አብሮነትና መቀራረብ ይበልጥ እንዲጎለብት ቤተ-እምነቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው አብሮነትና መቀራረብ ይበልጥ እንዲጎለብት ቤተ-እምነቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 27/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው አብሮነትና መቀራረብ ይበልጥ እንዲጎለብት ሁሉም ቤተ-እምነቶች ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡
"አሜን ኢትዮጵያ" የተሰኘው ድርጅት "የሰው ልጆች ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዓለም ሰላምና አብሮ ለመኖር" ቀንን ዛሬ አክብሯል።
በመርሃ-ግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡
የ"አሜን ኢትዮጵያ" መስራች ከሆኑት መካከል አባ ቄጥሮስ በርጋ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ጽንሰ ሃሳብ የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑን አንስተው፤ ይህንን እሴት አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
በዚህም አንዳችን ለሌላችን በማሰብ የእርስ በእርስ መረዳዳትና መተሳሰብን ማጎልበት አለብን ነው ያሉት፡፡
የዜጎች አብሮነትና መቀራረብ ለምጣኔ ሃብት፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካና ሌሎች ዘርፎች መጠናከር መሰረት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች በእምነት ተቋማቸው እንዲሁም ምሁራን በእሳቤያቸው በዜጎች መካከል መቀራረብን ለማጎልበት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ ዜጋ "እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት" በሚል አገሩን በማገዝ እንዲሁም ለዘላቂ አብሮነትና ሰላም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው በኢትዮጵያዊያን መካከል የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት እንዲጎለብት ሁሉም ቤተ-እምነቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ አኳያ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም ነው ያረጋገጡት፡፡
የአዲስ አበባና የጉራጌ ዞን አገረ-ስብከት ሊቀ-ጳጳስና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ ኢትዮጵያዊያን በርካታ የጋራ እሴቶች እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ቤተ-እምነቶች ይህን በመገንዘብ በኢትዮጵያዊያን መካከል መቀራረብና አብሮነት እንዲጎለብት እንዲሰሩም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው ህዝቡ የሃይማኖት አባቶችን ምክር እንዲያደምጥ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለውን አብሮነት የማጎልበቱ ስራ የሁሉንም ዜጎች ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
"የሰው ልጆች ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዓለም ሰላምና አብሮ ለመኖር" ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡