ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካን የግብርና ልማት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካን የግብርና ልማት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ነገ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካን የግብርና ልማት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 እስከ 2025 ድረስ በግብርና መስክ እምርታ ለማምጣት የሚያስችል ዓላማ ያለው የማላቡ ሥምምነት በመተግበር ላይ ይገኛል።
ሥምምነቱን ውጤታማ ለማድረግ የተዘጋጀው ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ዕድገት መርኃ ግብር (ካድፕ) ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው።
በነገው ዕለት በሚካሄደው የኅብረቱ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በሊቀ-መንበርነት የምትመራው የዚሁ የሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ዕድገት መርኃ ግብር (ካድፕ) አፈጻጸም ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህንንም ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀርቡታል ተብሎ እንደሚጠበቅ በኅብረቱ የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ ከባቢ ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካድፕ መርኃ ግብር በአፍሪካ አህጉር የተቀመጡ የግብርና መስክ ዕቅዶች አፈጻጸም የሚገኝበትን ደረጃ፤ የተገኙ ውጤቶችም ጭምር ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ረሃብን ከአፍሪካ ለማጥፋት የተያዘው ዕቅድ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም የድህነት ቅነሳ ተግባራት፣ የግብርና ምርት ንግድ ልውውጥ፣ የግብርና ዘርፍ ኢንቨስትመንት፣ ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋ የማይበገር ጠንካራ የምግብ ሥርዓት ግንባታ ላይ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ የተሰሩ ሥራዎችን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሪፖርቱን ተከትሎ አገራት በተያዘው ፈረንጆች ዓመት በአፍሪካ የምግብ ሥርዓትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ኮሚሽነራ ገልጸዋል።