በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የአባል አገራት መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የአባል አገራት መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥር 27/2014(ኢዜአ) በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የአባል አገራት መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ቀደም ሲል ከገቡት የተለያዩ አገራት መሪዎች በተጨማሪ የሲሸልስ ፕሬዘዳንት ዌቭል ራምካልዋን እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ዌቭል ራምካልዋን ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ፤ በተመሳሳይ ኤርፖርት ሲደርሱ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በአቀባበል ስነ-ስርአቱ ላይ የመከላከያ ማርች ባንድ፣ ከየክልሉ የመጡ የባህል ቡድን አባላት እንዲሁም የሰርከስ ትርኢት የሚያሳዩ ወጣቶች የተለያዩ ዝግጅቶችን አቅርበዋል።
ጉባኤውን ለመታደም ከትናንት ምሽት ጀምሮ የዘጠኝ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፤ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል” በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳል።