ቀጥታ፡

ግምታቸው ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

ሰመራ ጥር 27/2014(ኢዜአ) ባለፉት ሁለት ቀናት ግምታቸው ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የአዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የኮንትሮባንድ መከላከል ቡድን መሪ ኢንስፔክተር ዓለሙ ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት ጨለማን ተገን በማድረግ ወደ መሃል አገር ለማስገባት ሲሞከር ነው።

ጽህፈት ቤቱ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው እንቅስቃሴ ከምሥራቁ የአገሪቱ ክፍሎች ሲጓጓዙ የነበሩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ተናግረዋል።  


ጥር 25 ቀን 2014 የሰሌዳ ቁጥሩ ከድ-3- 49659 እና ኮድ3-15748 ኢት የሆኑ ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች ግምታዊ ዋጋቸው  ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ልባሽ ጨርቆች፣አዳዲስ አልባሳትና መድሃኒት ጭነው ከሽኒሌ ዞን ሙሉ ወረዳ ወደ ገዋኔ ወረዳ በጉዞ ላይ እንዳሉ ከቀኑ11 ሰዓት ላይ ተይዘዋል።

ተሽከርካሪዎቹ የተያዙት የጫኑትን ህገወጥ ዕቃዎች ሐሰተኛ የጉምሩክ ሰነድና የጉምሩክ ማሸጊያ አዘጋጅተው ህጋዊ በማስመሰል ወደ መሃል አገር ሊያስገቡ ሲሞክሩ የአዋሽ ጉምሩክ፣ ከሰመራ ጉምሩክና ከፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር ባከናወነው ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ መሆኑን አስታውቀዋል።

አንዱ አሽከርካሪ ለጊዜው የተሰወረ ሲሆን፣ ሌላኛው አሽከርካሪም በሕግ ቁጥጥር ሥር ውሎ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ኢንስፔክተር ዓለሙ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ጥር 24 ቀን 2014 ምሽት 5 ሰአዓት ጨለማን ተገን በማድረግ የሰሌዳ ቁጥራቸው ኮድ-3-A56891 እና  ኮድ-3-B04795 አዲስ አበባ በሆኑ የጭነት ተሸከርካሪዎች ግምታዊ ዋጋቸው ብር 13ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ  ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት ከምስራቅ የአገሪቱ ክፍል በተለይም ከድሬዳዋ ና ጅጅጋ አካባቢ በመነሳት በኦሮሚያ ክልል ሚኤሶና ቦርዴዴ ወረዳዎች  አድርገው  ወደ መሃል አገር ሲጓጓዙ ለጉምሩክ  በደረሰ መረጃ መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የአዋሽ ጉምሩክ የኢንተለጀንስ ሠራተኞች ፣የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ ፖሊስ አባላት በጋራ በሰሩት ቅንጅታዊ ሥራ ዕቃዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኢንስፔክተር ዓለሙ አስረድተዋል፡፡

አሽከርካሪዎቹ ለጊዜው ከአካባቢው በመሰወራቸው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ቡድን መሪው ገልጸዋል።

በኮንትሮባንድ ከተያዙት ዕቃዎችም ውስጥ መድሃኒት፣ሲጋራዎችና አልባሳት እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

በሥራው ላይ ተሳትፎ ላደረጉ የጸጥታ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች  ኢንስፔክተር  ዓለሙ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም