ዩኒቨርሲቲዎቹ ግምታቸው ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ቁሶችን ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎቹ ግምታቸው ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ቁሶችን ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ አደረጉ
ደሴ (ኢዜአ) ጥር 26/2014---ዩኒቨርሲቲዎቹ በአሸባሪው ህወሓት የወደመውን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ቁሶች ድጋፍ አደረጉ።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ካምፓስ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የጅማ እና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ኢንጂነር ጀማል ወርቁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት አገር ለማፍረስ አልሞ በከፈተው ጦርነት ያደረሰውን ሁለንተናዊ ጉዳትና ጫና በጋራ መመከት ያስፈልጋል።
ዩኒቨርሲቲው በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በሚችለው አቅም ሁሉ እንደሚያግዝም አረጋግጠዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲን ሥራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝም 10 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ዛሬ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
በእዚህም ለተማሪዎች ክሊኒክ፣ መመገቢያ፣ መማሪያና ማደሪያ ሕንጻዎች የሚሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ለአስተዳደር ሠራተኞች መገልገያ የሚሆኑ የጽህፈት መሳሪያዎችና መሰል ግብአቶችን መለገሳቸውን አስረድተዋል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ዶክተር ሰለሞን ጥሩነህ በበኩላቸው "ወሎ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ሥራ እንዲጀምር የምናደርገውን እገዛ እናጠናክራለን" ብለዋል።
በዚህም ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
በድጋፉ ኮምፒውተር፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የጽህፈት መሳሪያዎች፣ የሕክምናና ሌሎች ቁሶች እንደተካተቱና ድጋፉም ቀጣይነት እንዳለው አመልክተዋል።
ግምታቸው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ ቁሶችን መለገሳቸው የተናገሩት ደግሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አቶ ጢሶ ጎበና ናቸው።
በወሎ ዩኒቨርሲቲው ፍላጎት መሰረት የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስጀመር የሚያግዙ ቁሶችን ድጋፍ እንዳደረጉም ነው የተናገሩት
"አሸባሪው ህወሓት ዩኒቨርሲቲውን መሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አውድሞታል" ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲውን መልሶ በማቋቋም በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራውን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ 13 ዩኒቨርሲቲዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ ዛሬ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ መለገሳቸውን ገልጸዋል።
በድጋፉ ትምህርት ለመጀመር በቀዳሚነት የሚያስፈልጉ ቁሶች ማካተታቸውን ገልጸው፣ ይህም የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ ዶክተር አወል አመስግነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ተቋማት እያደረጉ ያለውን ሁለተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ጉዳት ከመድረሱ በፊት በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር እንደነበር ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።