ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ "ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ተናገሩ፡፡

35ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ "የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፤ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል'' በሚል መሪ ሃሳብ በመጪው ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳል።

በዛሬው እለትም የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ በጉባኤ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ሲገቡ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፤ ጉባኤውን በተሳካ መልኩ ለማከናወን የተለያዩ ተቋማትን ያካተተ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ እውነት ጎን በመቆም አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በተግባር ማሳየታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያም ጉባኤውን በስኬት ለማከናወን አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አድርጋ እንግዶቿን እየተቀበለች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ አፍሪካዊያን ከጎኗ በመሆን አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ጠቅሰው ጉባኤው አፍሪካዊ ወንድማማችነት የሚጠናከርበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በጉባኤው ለመሳተፍ አዲስ አበባ በመግባት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እንዲሁም የኮትዲቯር ፕሬዝዳንቶችና የጋምቢያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም