አየር መንገዱ ከስፔን ወደ ኮሎምቢያ አዲስ የካርጎ አገልግሎት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ከስፔን ወደ ኮሎምቢያ አዲስ የካርጎ አገልግሎት ጀመረ
አዲስ አበባ ነሃሴ25/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከስፔን ዛራጎዛ ወደ ኮሎምቢያ ቦጎታ አዲስ የካርጎ (የዕቃ ጭነት) የበረራ አገልግሎት ጀመረ። በረራው በቦይንግ 777 አውሮፕላን ከዛራጎዛ በሚያሚ ቦጎታ እንደሚሆን የተናገሩት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ ዛራጎዛ፣ ሚያሚና ቦጎታ የካርጎ አገልግሎት መረብን ስለተቀላቀሉ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል። በካርጎ አገልግሎቱ አየር መንገዱ ጥራት ያላቸው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ከዛራጎዛ ወደ ኮሎምቢያ በሣምንት ሁለት ጊዜ ለማጓጓዝ ያስችላል ብለዋል። አየር መንገዱ አንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 የካርጎ አገልግሎት መዳረሻውን እያሰፋ ለመሄድ የሚያደርግውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ያግዛልም ነው ያሉት። በዚህም የንግድና የምጣኔ ሃብትን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለማሳደግ እንደሚረዳ አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካ፣ በአረብ ባህረ ሰላጤ አገራት፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእስያና በአውሮፓ 44 መዳረሻዎች አሉት። ይህም አየር መንገዱን በአፍሪካ ትልቁ ድንበር ተሻጋሪ የካርጎ አገልግሎት ሰጪ እንደሚያደርገውና በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የማጓጓዝ አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።