ቀጥታ፡

ሚኒስቴሮቹ በአማራ ክልል በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የ14 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

ባህር ዳር፣ ጥር 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪዎቻቸውን ጨምሮ በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተጎዱ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት የ14 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።

ሚኒስቴሮቹ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ድጋፉን አስረክበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በወቅቱ እንደገለጹት፤ እየተደረገ ያለው ድጋፍ የኢትዮጵያዊያን አንድነት መሰረት ነው።

"የአሸባሪው ህወሃት አገር የማፍረስና የማተራመስ ዓላማ በወገን ጦር እርምጃ ከሽፏል" ብለዋል።

ቡድኑ ያደረሰው የሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ውድመት ከፍተኛና ጠባሳውም በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነ ገልፀው፤ ቡድኑ በክልሉ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ያደረሰው የውድመት መጠን እየተጠና መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በህልውና ዘመቻው ያሳየውን መተባበር አሁን ላይ በመልሶ ግንባታና ማቋቋም እየደገመው መሆኑን ጠቅሰው፤ ሚኒስቴሮቹ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው በክልሉ ከደረሰው ችግር ስፋት አንፃር በቀጣይም ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ህዝብንና አገርን ችግር ውስጥ ከቶ ለማጎሳቆል የተነሳ የጥፋት ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።

"ቡድኑ በተወሰደበት ጠንካራ እርምጃ ህልሙ ቢከሽፍም በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ላይ ያሳደረው ጉዳትና ጥፋት ተጨማሪ የቤት ሥራ ሆኗል" ብለዋል።

በአሸባሪው የደረሰውን ጉዳት ተጋግዞ ማለፍ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዛሬው እለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹና ተጠሪ ተቋማት  በጥሬ ገንዘብ የ10 ሚሊዮን ብርና  4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም