የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የምግብ ስርአት ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ለመቋቋም የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል

40

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የምግብ ስርአት ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ለመቋቋም የተቀናጀ ጥረት የሚያስፈልግ መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የገጠር ልማትና ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ገለጹ።

የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው እለትም ቀጥሎ እየተካሄደ ሲሆን ኮሚሽነሮችም በተጓዳኝ መግለጫ እየሰጡ ይገኛል።

በህብረቱ የገጠር ልማትና ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፤ በሰጡት መግለጫ በአህጉሪቷ በድህረ ኮቪድ -19 በፍጥነት ማገገም የሚቻልበትን የምግብ ስርአት ለመገንባት መወሰድ ያለባቸውን የመፍትሄ እርምጃዎች አመላክተዋል።

የወረርሽኙ መስፋፋት በግብርና፣ ቱሪዝምና ሌሎች የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ላይ ባሳደረው ተጽእኖ በርካቶች ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውን አብራርተዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ከ200 ሚሊዮን በላይ አፍሪካዊያን ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደነበር ኮሚሽነሯ አስታውሰዋል።

በአፍሪካ ባለፉት ሁለት አመታት በወረርሽኙ ሳቢያ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውንም ጠቅሰው አሁን ላይ ደግሞ ከ270 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል ብለዋል።

በመሆኑም ከዚህ ችግር ለመውጣት በአፍሪካ የተለየ የምግብ ስርአት ያስፈልጋል ብለዋል።

አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በተቀናጀ መንገድ መጠቀም አንደኛው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመው በግብርና፤ በንግድ እና ሌሎች ዘርፎችም ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት በሆነው ግብርና 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ኑሮውን የሚመራ ቢሆንም አገራት ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት እምብዛም መሆኑን ገልጸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይ የተጠናከረ የግብርና ስራ ያስፈልጋል ።

በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመቋቋም መወሰድ ያለባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች ላይም ኮሚሽነሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የአፍሪካ አስተዋጽኦ 4 በመቶ ቢሆንም ከተጽእኖ እንዳልወጣች ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ትላንት የተጀመረው የአፍሪካ ህብረት 40ኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም