አርብቶ አደሮችን ከገጠማቸው ችግር ለማሻገር እየታየ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድነትና የመደጋገፍ ባህል የሚያኮራ ነው

65

ድሬዳዋ፣ ጥር 26/2014(ኢዜአ)-በሱማሌ ክልል የድርቅ ተጎጂ አርብቶ አደሮችን ከገጠማቸው ችግር ለማሻገር እየታየ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድነትና የመደጋገፍ ባህል የሚያኮራ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ገለጹ።

በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች ግሎባል አሊያንስ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ  ድጋፍ ትናንት አድርጓል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ዩሱፍ ድጋፉን በተረከቡበት ጊዜ እንዳሉት የክልሉ መንግሥት በድርቅ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው አርብቶ አደሮችን ካጋጠማቸው ችግር ለማሻገር  በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው።

የደረሰውን ችግር በተባበረ ኢትዮጵያዊ አንድነትና የመደጋገፍ ባህል ለመሻገር እየተደረገ ያለው ርብርብ የሚያኮራና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት ደቅኖት የነበረውን የሕልውና አደጋ በተባበረ ክንድ ያመከነው መላው ኢትዮጵያዊ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለማሻገር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ።

በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች ድጋፍ ላደረጉት ግሎባል አሊያንስ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችንና ባለሃብቶችን አመስግነዋል።

ግሎባል አሊያንስ ትናንት ለድርቅ ተጎጂዎች ያበረከተው ድጋፍ 580 ካርቶን የምግብ ዘይት እና 900 ኩንታል የዳቦ ዱቄትን ያካተተ ነው።

የግሎባል አሊያንስ መስራች አርቲስት ታማኝ በየነ  በዚሁ ጊዜ እንዳለው የተደረገው ድጋፍ ከተከሰተው አደጋ አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው።

ግሎባል አሊያንስ  በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በማስተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።

በሶማሌ ክልል በዝናብ እጥረት በተከሰተ የድርቅ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለችግር መጋለጡንና የቤት እንስሳትም ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ቅነሳ ማስተባበሪያ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም