ከዘመቻው ጎን ለጎን ከ158 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል

82

መተማ፤ ጥር 26/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን ከ158 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የምእራብ ጎንደር ዞን ገቢዎች መመሪያ አስታውቀ።

በመምሪያው የግብር አሰባሰብና ክትትል ተወካይ ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው ዓመት ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ የገቢ አሰባሰብ ችግር ይገጥማል የሚል እሳቤ ነበር።

በተቀናጀ አግባብ በተሰራ ስራ በዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 313 ሚሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት የእቅዱን ከ50 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በግማሽ አመቱ 140 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚሆነው  ከመደበኛ ገቢ የተገኘ ሲሆን 17 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር  ደግሞ  ከከተማ አገልግሎት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ከእቅድ በላይ  ማሳካት መቻሉን አመልክተው፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ17 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

አካባቢው አለመረጋጋትና የሰላም እጦት የታየበት ቢሆንም የተገኘው የገቢ እድገት የግብር ከፋዩ ግንዛቤ መሻሻሉንና የተቋሙ ሰራተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት ያደረጉት አስተዋፅኦ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።

"በቀጣይም እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ተሞክሮዎቹን በማስፋት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በገንዳ ውሃ ከተማ በሆቴል ስራ የተሰማሩ ወይዘሮ የሺ መብራቱ እንደገለጹት የተጣለባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

''ግብርን በወቅቱ መክፈልም አንዱ ግንባር መሆኑን ተገንዝቢያለሁ'' ያሉት ነጋዴዋ በሆቴል ንግድ ከተጣለባቸው ግብር በተጨማሪ በከተማዋ ካላቸው ቤት በኪራይ ከሚያገኙት ገቢም ከ7 ሺህ ብር በላይ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

በህንፃ መሳሪያዎች ንግድ የተሰማሩት አቶ ቢኒያም አወቀ በበኩላቸው ነግደው ከሚያተርፉት ገቢ የሚጠበቅባቸውን ግብር መከፈላቸውን ገልጸዋል።

''የተጨማሪ እሴት ታክስን በታማኝነት በመሰብሰብ መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ እያስገኘሁ ነው'' ያሉት ነጋዴው፤ የገቢ ግብር ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትልም የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ በጀት አመት ከ150 ሺህ ብር በላይ ግብር መክፈላቸውን ጠቁመው፤ ወቅቱን ጠብቀው  መክፈላቸው በተጨማሪ ከወለድ እዳ ነፃ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዞኑ ባለፈው በጀት አመት 247 ሚሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ ለአካባቢው የልማት ስራ መዋል እንደተቻለ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም