ቀጥታ፡

ለእውቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የህይወት ዘመን ሽልማት ተሰጠ

አዲስ አበባ ነሃሴ 25/2010 የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ለታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የህይወት ዘመን ሽልማት ትናንት አበረከተ። ማህበሩ የ2010 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ጋዜጠኛ ፍቅሩ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ስፖርት ዕድገት ላይ ላበረከተው አስተዋጽኦ የህይወት ዘመን ሽልማት አግኝቷል። ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ ከ50 ዓመት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት፣ በአመራር እና በአማካሪነት የሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሲቋቋም በዋና ጸሐፊነት አገልግሏል፡፡ በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ካቢኔ ዳይሬክተር፣ የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተርና የኦሎምፒክ ሪቪው ዋና አዘጋጅ በመሆን ለረጅም ጊዜ ሰርቷል። የስፖርት ጋዜጠኝነትን የጀመረው በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ሲሆን ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ጭምር የስፖርት ዘገባዎችን ይጽፍ ነበር። የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲመሠረት የመጀመሪያ የሬዲዮ ስፖርት ጋዜጠኛ ሆኖ የሰራው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በስፖርት ጋዜጠኝነት አገልግሏል። ጋዜጠኛ ፍቅሩ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እንዲመሠረት እንዲሁም የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ዘመናዊ አደረጃጀት እንዲይዙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ካበረከተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለአፍሪካ ስፖርት እና ፕሬስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከቱ ከኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የህይወት ዘመን ሽልማት አግኝቷል። እውቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ለማህበሩ በላከው መልዕክት ለተበረከተለት ሽልማት ምስጋና በማቅረብ ጋዜጠኞች ለሙያቸው ታማኝ በመሆን ለስፖርቱ ዕድገት ተግተው እንዲሰሩ ጠይቋል። በዘርፉ የሚታዩ ሙስናና አድሎአዊ አሰራር ለማስወገድ የሙያ ማህበሩ በመታገል ሙያውን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል። ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ከአልጄሪያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርና ከዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ሽልማት እንዳገኘ መረጃዎች ይጠቁማሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም