የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ያሳረፈውን ችግር ለማቃለል በጋራ ሲሰራ ቆይቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ያሳረፈውን ችግር ለማቃለል በጋራ ሲሰራ ቆይቷል
ጥር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ያሳደረውን ችግር ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመፍትሄ ኃሳቦች ላይ ሲሰራ መቆየቱን የአፍሪካ ኅብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ዶክተር አቦዜይድ አማኒ ገለጹ።
ዶክተር አቦዜይድ አማኒ በአህጉሪቱ በመሰረተ ልማት ዘርፍ የትራንስፖርት፤ ኢነርጂና ዲጂታላይዜሽን ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአህጉሪቱ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ መጠነ ሰፊ ተጽእኖ ማሰረፉን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካ አየር መንገዶች ወርሃዊ የ2021 የመንገደኞች ገቢ ከ2019 ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች ስራ እስከማቆም ተደርሶ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
አየር መንገዶች ከገጠማቸው ችግሮች እንዲያገግሙ የተለያዩ እንቀሰቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደነበርም አንስተዋል።
"ችግሩን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአፍሪካ ሀገራት የአየር ትራንስፖረት ዘረፍ ላይ ስንሰራ ቆይተናል" ያሉት ኮሚሽነሯ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) ጨምሮ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአህጉሪቱ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሚሊዮን ያላነሱ አፍሪካዊያን የኃይል አቅርቦት የላቸውም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 900 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ምግብ የሚያበስሉበት ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጪ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀይል አቅርቦት በኩል የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍም የአንድ ቋት የኤሌክትሪክ ገበያ አገልግሎት በመላው አፍሪካ እንዲዳረስ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል። በተጓዳኝም አህጉሪቷን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።