የጤና ሚኒስቴር በአለታ ወንዶ ከተማ ከ600 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያደሳቸውን የአቅመ ደካሞች ቤት አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ሚኒስቴር በአለታ ወንዶ ከተማ ከ600 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያደሳቸውን የአቅመ ደካሞች ቤት አስረከበ

ሀዋሳ፤ ጥር 25/2014 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ከተማ ከ600 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያደሳቸውን የአቅመ ደካሞች ቤት አስረከበ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ከተማ በመገኘት ሚኒስቴሩ ያሳደሳቸውን ስድስት መኖሪያ ቤቶችን ትናንት አስረክበዋል።
ዶክተር ደረጀ በዚህ ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ የጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር ዐቢይን ጥሪ ተቀብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት እየተንቀሳቀሰ ነው።
የበጎ ፈቃድ ሥራውን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በመደገፍ መጀመሩን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 16 ቤቶችን በማደስ ከ75 በላይ ነዋሪዎችን ችግር ማቃለል መቻሉን ጠቁመዋል።
ጅምር ተግባሩን በማጠናከር በአለታ ወንዶ ከተማ ከ600 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ስድስት ቤቶችን ማሳደሱን አመልክተዋል።
በእድሳቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ህይወታቸውን ሲገፉ ለነበሩ 30 የቤተሰብ አባላት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
ቤታቸው ለታደሰላቸው ቤተሰቦች ሶፋ ፣ አልጋና ሌሎችንም መሰረታዊ የቤት ቁሳቁሶችን በማሟላት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በመንግሥት የተጀመረውን በጎ ተግባር በማጠናከር በቀጣይ መሰል ድጋፎችን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ቤታቸው ከታደሰላቸው መካከል ወይዘሮ አስቴር ባባ ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ ከሶስት ልጆቻቸውና ከአንድ የልጃቸው ልጅ ጋር በድህነት ለመኖር ተገደዋል።
በዚህም ላይ ያረጀው መኖሪያ ቤታቸውን ማደስ ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ችግር መዳረጋቸውን የተናገሩት ወይዘሮ አስቴር መኖሪያ ቤታቸው ከመታደሱ በፊት ግድግዳው የፈራረሰ ፣ቆርቆሮውም በየአቅጣጫው የሚያፈስ ስለነበር አስቸጋሪ ኑሮ ለመግፋት ተገደው እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ችግሩ ተወግዶ በተስተካከለና ባማረ ቤት ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር መኖር በመጀመራቸው እጅግ መደሰታቸውን በመግለጽ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
ወይዘሮ አልማዝ ገመዳ በበኩላቸው ባለቤታቸው በሕይወት እያሉም ህይወታቸውን በችግር ሲገፉ እንደነበር ጠቅሰው በሞት ካጧቸው በኋላ ችግራቸው እንደተባባሰ ተናግረዋል።
በጤና ህመም ከምትሰቃይ አንድ ሴትና ከሶስት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር በፈራረሰና በዘመመ ቤት ውስጥ የድህነት ህይወት ሲገፉ መቆየታቸውን የገለፁት ወይዘሮ አልማዝ በተለይ በዝናብ ወቅት ችግሩ የከፋ እንደነበር አስታውሰዋል።
ቤታቸው በመታደሱ ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው ገልፀዋል።
የአለታ ወንዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዳሁን ጋቢሶ በበኩላቸው ጤና ሚኒስቴር በከተማዋ ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ቤተሰቦች ስላከናወነው በጎ ሥራ አመስግነዋል።
ከነዚህ ቤቶች ውጪ በከተማው በተከናወኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች አምስት ቤቶች ታድሰው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰዋል።
ቤታቸው የታደሰላቸውን ቤተሰቦች ሕይወት በዘላቂነት ለማሻሻል ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስቴርና የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ አመራር አካላት ተገኝተዋል።