ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በማህበረሰብ የሬድዮ ጣቢያዎች ላይ 27 ሚሊየን ብር የሚገመት ውድመት አድርሷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 25/2014/ኢዜአ/   አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በማህበረሰብ የሬድዮ ጣቢያዎች ላይ 27 ሚሊየን ብር የሚገመት ውድመት ማድረሱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ፤ ባለስልጣኑ ሬድዮና ቴሌቭዥን ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች የማህበረሰብ ሬድዮ እንዲኖራቸው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በብሮድካስት፣ በህትመት እና በበይነ መረብ ለሚሰሩ ሁሉ የፈቃድ እና ምዝገባ ስራ በማከናወን የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትን እያስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።።

በኢትዮጵያ እስካሁን ለ54 የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ፍቃድ በመስጠት ከእነዚህ መካከል 32ቱ ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።

ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትን የማስፋት ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የጠቀሱት አቶ ግዛው፤ አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ያካሄደባቸው የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በማህበረሰብ የሬድዮ ጣቢያዎች ላይ 27 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል ብለዋል።

ባለስልጣኑ የጥናት ቡድን ወደ ስፍራው በመላክ የደረሰውን የውድመት መጠን ማረጋገጡን ተናግረዋል።

በዚህም በኮምቦልቻ፣ በዋግህምራ እና በወልዲያ ከተሞች የነበሩ ሶስት የማህረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።

የስቱዲዮ መሳሪያዎች የማሰራጫ መሳሪያዎች እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦታቸው ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሬድዮ ጣቢያዎቹ ማህበረሰቡን በማስተማር እና መረጃ በመስጠት ትልቅ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰው በአሸባሪው ህወሃት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል ነው ያሉት።

ሆኖም ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ጣቢያዎቹን በመልሶ ግንባታ አገልግሎት ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም