ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ጭምር አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የመንገድ ምርምር ማእከል በመገንባት ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ጭምር አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የመንገድ ምርምር ማእከል በመገንባት ላይ ነው
አዲስ አበባ ነሀሴ 24/2010 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ጭምር አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የመንገድ ምርምር ማእከል በአራት ሚሊዮን ብር ወጪ በማስገንባት ላይ መሆኑን አስታወቀ። የባለሰልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ይህን ያስታወቁት ዛሬ በተጀመረው አምስተኛው የመንገድ ምርምር ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቆ እየተገነባ ያለው ማእከሉ ከመንገድ ልማት ጋር በተያያዘ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት፣ በኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማሻሻል የሚያግዙ አዳዲስ ሀሳቦችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማመንጨት ያስችላል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ግንባታው በአዲሰ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ማእከሉ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በመጪው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት የህንፃው ሲቪል ሥራ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ሜካኒካል ነክ የሆነው የፕሮጀክቱ ሥራም መጀመሩ ተገልጿል።