ቀጥታ፡

ለአፍሪካ የተለያዩ ተቋማትና ኤምባሲዎች የተሰጡ ቦታዎች በፍጥነት ወደ ግንባታ እንዲገቡ ኢትዮጵያ አስፈላጊው ድጋፍ ታደርጋለች

ጥር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአፍሪካ የተለያዩ ተቋማትና ኤምባሲዎች የተሰጡ ቦታዎች በፍጥነት ወደ ግንባታ እንዲገቡ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሜኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ መካሄድ የጀመረውን 40ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ ጉባኤው በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከረ ነው።

በአህህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት፣ በኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአጀንዳ 2063 አፈጻጸም እንዲሁም በበጀት አጠቃቀም ዙሪያ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።

ለአፍሪካ የተለያዩ ተቋማትና ኤምባሲዎች የተሰጡ ቦታዎች በፍጥነት ወደ ግንባታ እንዲገቡ በኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መተላለፉን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና፤ በፍጥነት ወደ ግንባታ እንዲገቡ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ጽሁፍ ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጧን ጠቅሰዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነትም ተፈጸመ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቋም ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጥምረት ማጣራቱን አስታውሰዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም