ቀጥታ፡

አፍሪካ የሚገጥሟትን ችግሮች ለመቅረፍ በመንግሥትና በግል ሴክተሮች ላይ የሚካሄዱ ትብብሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው

አዲስ አበባ፣ ጥር 25/2014/ኢዜአ/  አፍሪካ አሁን የሚገጥሟትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ በመንግሥትና በግል ሴክተሮች ላይ የሚካሄዱ ትብብሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የአፍሪካ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች 40ኛው መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

በስብሰባው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ቬራ ሶንግዌ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአፍሪካ በኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰው፤ ተጽዕኖውን ለመከላከል የወጣው የኢኮኖሚ ወጪ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ የብድር ምጣኔ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር ከዚህ ቀደም 40 በመቶ የነበረው አሁን ላይ 70 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።  

በተመሳሳይ በ2014 ዓ.ም የብድር ጫና ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ከነበሩ 17 አገራት መካከል አራቱ የእዳ ጫና ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪ ወረርሽኙ በአህጉሪቷ ላይ የስርዓተ ምግብ ችግር እንዲባባስ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም አፍሪካ ከዘላቂ የልማት ግቦች መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን "ርሃብን ማጥፋትና ዓመቱን ሙሉ የምግብ ተደራሽነት ማረጋገጥ" የሚለውን ማሳካት የምትችልበት ደረጃ ላይ አለመሆኗን ጠቁመዋል።

ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት በአህጉሪቷ 282 ሚሊዮን ሰዎች ለርሃብ መዳረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም አፍሪካ በመቀንጨር ምክንያት በየዓመቱ ከ3 እስከ 16 በመቶ አጠቃላይ አገራዊ ምርት እንደምታጣም ገልጸዋል።

እነዚህም አጠቃላይ ችግሮች የሚያሳዩት አፍሪካ የተለያዩ ችግሮችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት እንዳለባትና ችግሮቹንም ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋት  መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ የሚከሰቱ ሳይበር ደህንነት ጥቃት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ወረርሽኝና ተላላፊ በሽታዎች አሁንም አህጉሪቱን እየፈተኗት በመሆኑ የምትቋቋምበት አቅም መፍጠር እንዳለባት አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ አፍሪካ በመንግሥትና በግል ሴክተሩ የሚካሄዱ ትብብሮች ተጠናክረውና ተስፋፍተው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይም ደግሞ አየር ንብረትን የሚቋቋም ግብርና፣ የገበያ ተደራሽነትና ምቹ የቢዝነስ አካባቢን መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሊካሄድ ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እና መሰል ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም