የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳዎችና ውሳኔዎችን ተደራሽ በማድረግ ሚዲያዎች ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳዎችና ውሳኔዎችን ተደራሽ በማድረግ ሚዲያዎች ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት አለባቸው
ጥር 25/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳዎችና ውሳኔዎችን ተደራሽ በማድረግ ሚዲያዎች ያለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ ተናገሩ።
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።
የመሪዎቹ ጉባኤ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ሲካሄድ 40ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ ዛሬና ነገ ይካሄዳል።
ጉባኤውን ለመዘገብ ከ300 በላይ የሃገር ውስጥ እና ከ200 በላይ የውጭ አገር ጋዜጠኞች ባጅ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን መግለጹ ይታወቃል።
በመሆኑም በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ ለዘገባ የተሰማሩ ጋዜጠኞች የህብረቱን አጀንዳዎችና ውሳኔዎች ተደራሽ በማድረግ ያለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃኑ የጉባኤውን ጭብጥና ውሳኔ በዜና እና በፕሮግራም ጭምር አጉልተው በመስራት ለዓለም ህዝብ እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት በርካታ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የተሳተፉባቸውን ሃይማኖታዊ በዓላት በአስተማማኝ ሰላም ማከናወኗን አስታውሰው የመሪዎቹን ጉባኤ በስኬት ማስተናገድ እንደምትችልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የዘንድሮው አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው ጉባኤው አፍሪካዊያን አንድነትና ህብረታቸውን አጠናክረው ይበልጥ የሚተባበሩበት መልካም አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል።
ለህብረቱ ጉባኤ ሰላማዊ ክንውን በተለመደው እንግዳ አቀባበላችን እንግዶችን ለማስተናገድ ልንዘጋጅ ይገባል ያሉት ዶክተር ደመላሽ፤ ሁላችንም የድርሻችንን ሃላፊነት እንወጣ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው 40ኛው የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ በዛሬው እለት ተጀምሯል።