ዳያስፖራው በግንባታና መሰረተ ልማት ዘርፍ በመሰማራት ለኢትዮጵያ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በግንባታና መሰረተ ልማት ዘርፍ በመሰማራት ለኢትዮጵያ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል
ጥር 24/2014/ኢዜአ/ ዳያስፖራው በግንባታና መሰረተ ልማት ዘርፍ በመሰማራት ለኢትዮጵያ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጉዳዩን በሚመለከት ከዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚህን ወቅት በኢትዮጵያ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቤቶችና መሰረተ ልማት ፍላጎት ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በ2020 ዓ.ም 18 ሺህ የገጠር ማዕከላት ወደ ከተማነት እንደሚያድጉ ጠቅሰው፤ በ2024 ዓ.ም በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ ህዝብ መካከል 35 በመቶ የሚሆነው በከተሞች ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ዳያስፖራው በቤቶች ልማት፣ በኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦት እና በሌሎች ተያያዥ መስኮች በመሳተፍ ከራሱ አልፎ አገሩን መጥቀም እንደሚችል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መስፍን ነገዎ በበኩላቸው መንግስት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በግምባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ፣ ተጨማሪ በጀት መጠየቅ፣ የጥራት መጓደል በዘርፉ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ዳያስፖራው በዘርፉ በመሰማራት ችግሮቹን በመቀነስ ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዳያስፖራው በዘርፉ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ከራሱ አልፎ አገርን ወደ ተሻለ ምእራፍ ማሸጋገር እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ኢድሪስ ናቸው።
በመድረኩ የተሳተፉ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ልማት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ የመንግስት የአሰራር ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡