ቀጥታ፡

ውስብስብ ችግሮችን አልፈን ብሔራዊ ፈተና መውሰድ መጀመራችን ተስፋችንን አለምልሟል

ደሴ፣ ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተፈጠሩ ውስብስብ ችግሮችን አልፈን ብሄራዊ ፈተና መውሰድ መጀመራችን ተስፋችንን አለምልሟል ሲሉ በደሴ ከተማ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና እየወሰዱ ያሉ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ያልወሰዱ 2 ሺህ 788 ተማሪዎች ዛሬ ፈተና ጀምረዋል፡፡

በደሴ ከተማ ሆጤ ፈተና ማዕከል ተፈታኝ የሆነችው ተማሪ ኅሊና ፈረደ ለኢዜአ እንደገለጸችው፤ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች።

ነገር ግን አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል ውስጥ ፈጽሞት በነበረው ወረራ ምክንያት ፈተናውን ያለመውሰድ ስጋት ገብቷት እንደነበር ገልጻ፤ አሁን ፈተናውን መውሰድ መጀመሯ ዳግም ተስፋ እንድትጨብጥ አድርጓታል።

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ለህጻናት፣ ለሴቶችና ለአዛውንቶች ሀዘኔታ እንደሌላቸው የገለጸችው ተማሪ ኅሊና፤ የጥቃት ሰለባ ላለመሆን ከመኖሪያ አካባቢዋ ተፈናቅላ የተለያዩ ችግሮችን ማስተናገዷን ገልጻለች።

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በወሰዱት የተቀናጀ እርምጃ አካባቢው ከወራሪው ኃይል ነፃ በመውጣቱ ብሔራዊ ፈተናውን መውሰድ መጀመሯ እንዳስደሰታትና ተስፋዋ እንዲለመልም እንዳደረጋት ተናግራለች።

''የፈተናው አስተባባሪዎችና ፈታኞችም ከቀደመው ጭንቀት ወጥተን በአዲስ መንፈስ ተረጋግተን እንድንፈትን ምክር  በመስጠት እያገዙን ነው'' ብላለች።

ሌላዋ ተፈታኝ ተማሪ መሰረት ያየህ በበኩሏ የፈተናው ቀን በየጊዜው መራዘሙ አሰልቺና ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደነበር አስታውሳ፤ ''ሁኔታዎች ተመቻችተው ዛሬ ፈተና መውሰድ በመጀመራችን የነገ ህይወታችንን ማሰብ እንጀምራለን" ብላለች።

የሆጤ ፈተና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ሰይድ ከበደ በበኩላቸው በማዕከሉ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች ፈተና እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው፤ ተፈታኞች ፈተናውን ተረጋግተው እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነት ቀደም ሲል የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ያልወሰዱ 2 ሺህ 788 ተማሪዎች ፈተና እየወሰዱ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ ገልጸዋል።

በሦስቱም የፈተና ማዕከሎች ለፈተናው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ቀደም ሲል በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች ተሟልተው በመድረሳቸው ፈተናው በጥሩ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።

ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የፀጥታ ስምሪት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም