ሀገራዊና ክልላዊ የብልፅግና ትልሞችን ለማሳካት አመራሩ በአገልጋይነት ስሜት ሊረባረብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊና ክልላዊ የብልፅግና ትልሞችን ለማሳካት አመራሩ በአገልጋይነት ስሜት ሊረባረብ ይገባል
ሚዛን፣ ጥር 24/2014 (ኢዜአ)...ሀገራዊና ክልላዊ የብልፅግና ትልሞችን ለማሳካት አመራሩ በአገልጋይነት ስሜት ሊረባረብ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስገነዘቡ።
"መመረጥ ተለውጦ ሀገርን ለመለወጥ በሚል" መሪ ሃሳብለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አመራሮች የውይይት መድረክ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተጀምሯል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የክልሉ ህዝብ በሚፈለገው ልክ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አመራሩ በለውጥ መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል።
መድረኩይህ እውን እንዲሆን እራሱ ተለውጦ ሀገርን የሚለውጥ አመራር እና አባላትን በየደረጃው ለማፍራት ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመድረኩ በመሳተፍ ላይ ያሉ አመራሮች ሀገራዊና ክልላዊ የብልፅግና ትልሞችን ለማሳካት በአገልጋይነት ስሜት ሊረባረቡ እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳሰበዋል።
በተለይ ትክክለኛ የብልፅግና አስተሳሰቦችንና መሠረታዊ መርሆዎችን ሁሉም አመራር ጠንቅቆ አውቆ ለተግባራዊነቱ እንዲንቀሳቀስም አስገንዝበዋል።
ለሀገር ለውጥና የብልፅግና ጉዞ ስኬት ብቁ የሰው ኃይል በመገንባት ራሱ በቅቶ ሌሎችን ማብቃት የሚችል አመራር ከምን ጊዜ በላይ ሀገሪቱ እንደሚያስፈልጋትም ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ አመልክተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ የመድረኩ ዓላማ የአመራሩን ቁመና ለይቶ ለብልዕግና ቀጣይ ጉዞ ስኬታማነት ብቁ አመራር መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገሪቱእስካሁን በተካሄደው የለውጥ ጉዞ የታዩ ክፍተቶችን በማረም ጠንካራ አመራር ለመገንባት የሚያስችል ውይይት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።