ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ የፓርቲውን መርሆዎች በአግባቡ የሚፈጽሙ አመራሮችን ይዞ እንደሚቀጥል አስታወቀ

ሀዋሳ ጥር 24/2014 (ኢዜአ) ከግል ጥቅመኝነት የጸዱና የፓርቲውን መርሆዎች በአግባቡ የመፈጸም አቅም ያላቸውን አመራሮች ይዞ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱን በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

"መመረጥ ተለውጦ ሀገርን ለመለወጥ" በሚል መሪ ሀሳብ የብልፅግና ፓርቲ ለሲዳማ ክልል ከፍተኛ  አመራሮች ለአራት ቀናት የተዘጋጀ የአመራር ግንባታ  መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በፓርቲው የሲዳማ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ  በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በሁሉም ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ህዝብን መርቶ ወደ ሚፈለገው ብልፅግና ሊያሸጋግር የሚችል አመራር ያስፈልጋል።

በተለይ የተለወጠ አመራር ህዝብን ለመለወጥና በብልፅግና ጉዞ ላይ መሰናክል የሚፈጥሩ ጉዳዮችን አጥርቶ በማለፍ ወደ ሚፈለገው ግብ ማድረስ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

"በዚህ ደረጃ ህዝብን አሳትፎ ከመስራት ይልቅ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አለመፍታት ጥቅመኝነት፣ ህዝብን በአግባቡ ያለማገልገል  በአመራሩ ዘንድ ተስተውሏል።" ብለዋል።

በአመራሩ የተስተዋሉ ተግዳሮቶችን ከመሠረቱ ለማስወገድ የአመራር ግንባታ ውይይት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ መስተካከል የሚችለው እንዲስተካከል፣ የማይስተካከለው ደግሞ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ እንዲሆን የማጥራት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ መርሆዎች የሆኑትን የወንድማማችነት፣ ዜጋን የማክበር፣ የሚፈልገውን አገልግሎት በአግባቡና በወቅቱ መስጠትና የልማት ውጥኖችን ማሳካት የሚችል አመራር ብቻ ይዞ ለመቀጠል ውጥን መያዙን አስታውቀዋል።

"ሰርጎ ገብ የሆነ ኃይል ተጠርጎ የሚወጣበት፣ ለህዝብ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በቀጣይነት ህዝቡን ሊያገለግል የሚችል አባልና አመራር ለማፍራት አቋም ተይዟል" ሲሉም  ተናግረዋል።

በመድረኩ "አመራሩ ህዝቡ የሰጠውን አደራ በአግባቡ እየተወጣ ነው፣ ማገልገል በሚገባው ልክ እያገለገለ ነው ፣ ምን ጉድለቶች አሉ፣ ምን ለውጥ አመጣን እና ለውጥ ያላመጣንባቸው  ነጥቦች ምንድን ናቸው" የሚሉ አንኳር ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እንደሚደረግባቸው አመልክተዋል።

ባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተከናወኑ ተግባራትም በመድረኩ እንደሚገመገሙ  ጠቁመዋል።

መድረኩ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውሰጥ ለማከናወን የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ጨምሮ በብሄራዊ  አጀንዳዎች ዙርያ በጥልቀት በመወያየት አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን አቶ አብርሃም አስረድተዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም በየደረጃው ከመካከለኛ አመራሩ እስከ ፓርቲው አባላት ድረስ  በአጀንዳዎቹ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸው፤ በዚህም  አመራሩ እራሱን  የሚፈትሽበት ይሆናል  ሲሉ ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም