አሚሶም በሶማሊያ ሠራዊት የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
አሚሶም በሶማሊያ ሠራዊት የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጓል
አዲስ አበባ ነሀሴ 24/2010 በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) በሶማሊያ ሠራዊት አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገለጸ። አሚሶም ከወራት በፊት የጀመረውን ሠራዊቱን ከሶማሊያ የማውጣት ሥራ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ምዕራፍ ይጠናቀቃል ብሏል። የአሚሶም ምክትል ኃላፊ ሲሞን ሙሎንጎ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት የሶማሊያን ሠላም የሚያደፈርሰው አልሸባብ በበርካታ ቦታዎች ላይ በእጅጉ ተዳክሟል። ለዚህም አሚሶም ያሰማራው ሠራዊት ያከናወናቸው ተግባራት መሆኑን ጠቁመው አሁን አልሸባብ ታጥቆ መዋጋት የሚችልበት አቅም አጥቷል ብለዋል። በዚህም የሶማሊያ ህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚጠቀምባቸው ስልቶች ሽብር መንዛትና የተቀመሙ የእጅ ቦንቦችን የማፈንዳት ሥራ ላይ መጠመዱን ገልጸዋል። አሚሶምም ይህንን ጉዳይ ከግምት በማስገባት የማጥራት ሥራ እየሰራ እንደሆነና ቀስ በቀስ የደህንነት ሥራውን ለሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ አስረክቦ ይወጣል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የአቅም ግንባታ ሥራ ለሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው አሚሶምም ከግዳጁ ውጪ ተልዕኮውን እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል። ቀደም ሲል የአሚሶም ከግዳጁ ውጪ በሌሎች ሥፍራዎች ትኩረት እንዲያደርግ ቢደረግም የሠራዊት ቁጥር ከቦታዎቹ ስፋት ጋር ባለመመጣጠኑ ሳይሳካ መቅረቱን ገልጸዋል። በመሆኑም አሁኑ ወቅት አሚሶም አቅሙን በመገምገም የሶማሊያን ሠላም ለማረጋገጥ ጥረት እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ለመጣው ሠላም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያከናወነው ተግባር ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸው ሠራዊቱ ሕዝባዊነቱን አረጋግጧል ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) የዛሬ 10 ዓመት ነበር በሶማሊያ ለሰድስት ወራት ሠላም ለማስከበር ወደ ሶማሊያ ያቀናው። ይሁንና በሶማሊያ ያለው ሠላም በቀላሉ ማረጋገጥ ባለመቻሉ ተጨማሪ ሠራዊት በመመደብ በተለያዩ ጊዜያት ቆይታውን በማራዘም እስከ አሁን ድረስ ግዳጅ ላይ ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከወራት በፊት አሚሶም ከሁለት ዓመት በኋላ ከሶማሊያ ቀስ በቀስ ለቆ እንዲወጣ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት በአሚሶም ከስደስት አፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ20 ሺህ በላይ የጦር ሠራዊቶች በሶማሊያ ይገኛሉ።